የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በመልስ ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ገጥሞ 1ለ0 ቢሸነፍም ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጨዋታ ባስመዘገበው ውጤት መሰረት በ3ለ1 ድምር ውጤት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ያለፈ ሲሆን ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅም በኋላ ተከታዩን አጭር ሀሳብ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ከጨዋታው በኋላ ሰጥቷል፡፡
ስለ ዛሬው ጨዋታ እና ስለ ታየው ድክመት
“በጨዋታው እንዳያችሁት ለመሸነፍ በቅተናል። ለማሸነፍ ትልቅ ጉጉት ውስጥ ተጫዋቾቼ ነበሩ፡፡ በተፈጠረው ስህተት ጎል ገብቶብናል፡፡ ከመጓጓት የተነሳ ነው ይህ ውጤት የተከሰተው፡፡ ከእረፍት በፊት የተሳቱ ኳሶችን አይታችኋል፡፡እና ያለ መረጋጋት ጎሉን ከገባ በኋላ የመረበሽ ነው እንጂ ሌላ ምንም ችግር የለም። ኳስን ይዘን አለመጫወትም ነው ችግሩ፡፡”
ከሜዳ ውጪ ጥሩ ሆኖ በራስ ሜዳ ላይ ስለ መዳከም
“እኔም ያልገባኝ ነገር እሱ ነው፡፡ ከሜዳ ውጪ በደንብ እንጫወታለን፡፡ ልምምድም ስንሰራ ነበር፡፡ በሚያውቁት ሀገር ነው የሚጫወቱት፤ በራሳቸው ሜዳ ነው፡፡ የሰራንበትም ሜዳ ነው፡፡ ያለውን ችግር ልናውቅ አልቻልንም፡፡ ቀጣይ ባሉን ጨዋታዎች ላይ ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከሜዳ ውጪ ያለው ስሜት እና በሜዳችን ያለው ስሜት አንድ አይነት አይደለም፡፡ እዚህ ላይ በደንብ አጠንክረን መስራት እንዳለብን የተማርንበት ነው፡፡
ስለ ቀጣይ ተጋጣሚዋ ናይጄሪያ
“ናይጄሪያ ጠንካራ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ አሁን የምናስበው ስለ ራሳችን ነው፡፡ እንዴት ነው ጠንካራ መሆን ያለብን የምንጫወተው ከሴቶች ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎቹን እንዳሸነፍን አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጥረት የምናደርገው ግን በተለይ ስህተቶቻችን ላይ ነው ትኩረት አድርገን የምንሰራው፡፡ ስለ ምንጫወተው ቡድን ብዙ የሚያሳስበን እና የሚያስጨንቀን አይደለም፡፡