ሪፖርት | አዝናኙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የ21ኛ የጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት የመጀመሪያ የነበረው እና ስድስት ግቦች የተቆጠሩበት አዝናኙ የአዲስ አበባ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

አዲስ አበባ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መሀመድ አበራን በአቤል ነጋሽ የተኩ ሲሆን በአንፃሩ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ ሀዋሳ ከተማን ከረታው ስብስብ አንድ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃንን በእያሱ ታምሩ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ጨዋታው ጅማሮውን ያደረገው በጎል ነበር ፤ 2ኛው ደቂቃ ሮቤል ግርማ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ተጠቅሞ እንዳለ ከበደ ወደ መሀል የላከው ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ ለመጠቀም ሲሞክር ፍሬዘር ካሳ በሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሪችሞንድ አስቆጥሮ አዲስ አበባን መሪ አድርጓል።

ጨዋታው ዳግም ወደ እንቅስቃሴ ሲመለስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች አቻ ለመሆን ብዙም ለመጠበቅ አልተገደዱም። 7ኛው ደቂቃ ላይ በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ ሳጥን ለመድረስ የሞከረው ብርሃኑ በቀለ ላይ አዩብ በቀታ በሰራው ጥፋት ምክንያት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳምሶን ጥላሁን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
አስገራሚ አጀማመር እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ አዲስ አበባ ከተማ ዳግም መሪ መሆን ችሏል። በቀኝ መስመር በኩል አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ሪችሞንድ አዶንጎ ወደ ሳጥን ይዞ ከደረሰ በኋላ ወደ መሀል ያቀበለውን ኳስ አቤል ነጋሽ ማስቆጠር ችሏል። 

በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተደጋጋሚ በፈጣን የኳስ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተሻለ ጥረት በማድረግ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። በተለይም በ22ኛው ደቂቃ አበባየሁ ዮሐንስ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ብርሃኑ በቀለ በግንባር በመግጨት የሞከረውን ኳስ ዳንኤል ተሾመ በግሩም ቅልጥፍና ያዳነበት ኳስ እጅግ አደገኛ አጋጣሚ ነበረች።
በ24ኛው ደቂቃ ታድያ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዳግም አቻ ሆነዋል። የአዲስ አበባ ከተማው ሙሉቀን አዲሱ በማቀበል ሂደት አደገኛ ስፍራ ላይ የሰራውን ስህተት ተጠቅመው ያገኙትን አጋጣሚ ሀብታሙ ታደሰ በተረጋጋ ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

በጨዋታው በመልሶ ማጥቃት አጥቅተው ለመጫወት ይታትሩ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ለቀው የሚወጡትን የሜዳ ክፍል ለማጥቃት ሲሞክሩ የተመለከትናቸው አዲስ አበባዎች አደገኛ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህ ሂደትም በ34ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች በጨዋታው ለሦስተኛ ጊዜ ወደ መሪነት መምጣት ችለዋል። የመሀል ተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙ የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመሀል ሜዳ አንስቶ በአስደናቂ ፍጥነት ኳሷን እየነዳ የሀዲያ ሳጥን የደረሰው አቤል ነጋሽ በግራ እግሩ እጅግ ማራኪ ግብን አስቆጥሯል።

እጅግ አስገራሚ በሆነ ፉክክር በቀለው ጨዋታ በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች እንዳለ ከበደ በአዲስ አበባ በኩል እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አደገኛ አጋጣሚዎችን አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ቴዎድሮስ ሀሙን አስወጥተው በምትኩ ዘሪሁን አንሼቦን በመተካት የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ እጃቸው የገባውን ነጥብ ለማስጠበቅ ይረዳቸው ዘንድ ከኳስ ውጪ ሲሆኑ ከፊት አጥቂያቸው ውጪ በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል ጥረት አድርገዋል።
በአንፃሩ የመስመር ተመላላሹን እያሱ ታምሩ አስወጥተው ባዬ ገዛኸኝን በማስገባት በሦስት አጥቂ አጋማሹን የጀመሩት ሀዲያዎች በአጋማሹ ጅማሮ ሮቤል ግርማ በስህተት ወደ ራሱ ግብ በግንባሩ ገጭቶ ከሞከራት ኳስ ውጪ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ተሰተውሏል።

በአጋማሹ በሆሳዕና በኩል የተደረገው ሌላኛው ሙከራ በ65ኛው ደቂቃ ሄኖክ አርፊጮ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ዘሪሁን አንሼቦ በስህተት ወደ ራሱ ግብ የገጨውን ኳስ በቀላሉ መቆጣጠር ያልቻለው ዳንኤል ተሾመ እንደምንም ብሎ ኳሱን ቢያድንም በሂደቱ ባስተናገደው ጉዳት መነሻነት በወንደሰን ገረመው ተተክቶ ወጥቷል።

ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በኤፍሬም ዘካርያስ ጥረት ከምንም ግብ አግኝተዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያዎች ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያገኙትን የቅጣት ምት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ዘካርያስ በወንደሰን ገረመው ስህተት ታግዞ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና ነጥቡን ወደ 29 እንዲሁም አዲስ አበባ ደግሞ ወደ 21 በማሳደግ በነበሩበት 6ኛ እና 14ኛ ደረጃ ቀጥለዋል።

ያጋሩ