የአሠልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 3-3 ሀዲያ ሆሳዕና

ስድስት ግቦች ከተቆጠሩበት አዝናኙ ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ሦስት ጊዜ መርተው አቻ ስለመለያየታቸው…?

እግርኳስ እንዲህ ነው። እኛ መጀመሪያ ይዘን የገባነው ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ነው። ስህተቶች ደግሞ ይፈጠራሉ። እነዛ ስህተቶች ደግሞ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል። ግን እንቅስቃሴያችን እንደፈለግነው ነው። ጥሩ ነው።

ሀዲያ ወደ ጨዋታ እንዲመለስ የሆነበት ምክንያት…?

ተከላካይ እና መሐል ላይ የተሰሩ ስህተቶች አሉ። የኳስ ባህሪው ነው እና ስህተቶች ይፈጠራሉ። እነሱን በፀጋ እንቀበላለን። ወደፊት ግን እርምት እንወስድባቸዋለን።

ስለመከላከል አጨዋወታቸው…?

በጨዋታው እኛ አላፈገፈግንም። ያለንበት ቦታ ጥሩ ስላልሆነ ማፈግፈግ አታስፈልግም። የግድ ማጥቃቱ ላይ ተጫውተን ይሄንን ደረጃችንን ማሻሻል አለብን። እርግጥ ብዙ ጨዋታዎች አሉ። ግን ማጥቃት ላይ ተመርኩዘን ነው የምንጫወተው። ስህተቶች ሲፈጠሩ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል።

ስለአቤል ብቃት…?

አቤል ጎበዝ ተጫዋች ነው። ወደፊት ደግሞ የተሻለ ነገር ይሰራል ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም ገና ወጣት ነው። እየጠበቅን ለማንቀሳቀስ ነው እንጂ ወደፊት ጥሩ ይሆናል።

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው…?

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከመመራት እያገባን ነው እኩል የወጣነው። ለሰው ደስ ይላል። እኛ ግን ባሰብነው እና ባቀድነው ነገር ባይሆንልንም ሜዳ ላይ ከነበሩት ነገሮች ጥሩ ነው። ብናሸንፍ የተሻለ ነው። ተቃራኒያችን ደግሞ ጠንካራ እና ያለበት ቦታ አስቸጋሪ ስለሆነ ተገቢ ነው ብዬ አስባለው።

በመከላከሉ በኩል ስለነበረባቸው ውስንነት…?

በማግባቱ በኩል ጥሩ ነው። ማግባት ጥሩ ጎን ስለሆነ ጥሩ ነው። በመከላከል ደግሞ ተከላካዮቹ በጣም ጥሩ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ከትኩረት ጋር በተገናኘ ስህተቶች ይፈጠራሉ። እሱን ደግሞ ቀስ እያልን እናስተካክላለን።