ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከመመራት ተነስተው አሸንፈዋል

የሊጉ የአዳማ ቆይታ የመጨረሻ እና በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር ትልቅ ትርጉም በነበረው መርሃግብር በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ የቀረበው ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ ከመሪው የነበረውን ልዮነት አጥቧል።

በአሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች አርባምንጭ ከተማን በጠባብ ውጤት ካሸነፈው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም አምሳሉ ጥላሁን እና ሽመክት ጉግሳን አስወጥተው በምትካቸው ያሬድ ባየህ እና ሰዒድ ሀሰንን ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያሙ ወላይታ ድቻ ደግሞ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አማካይ ክፍሉ ላይ አበባየሁ አጪሶን አስወጥተው በምትኩ እድሪስ ሰዒድን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

በርካታ ቁጥር ባላቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከወትሮው በተለየ አውንታዊ ሆነው የጀመሩበት ነበር በዚህም በተደጋጋሚ ወደ የፋሲልን ሳጥን ለመጎብኘት ጥረት አድርገዋል።

ባልተለመደ መልኩ በዛሬው ጨዋታ በኃላ ሦስት የመሀል ተከላካዮች ጨዋታውን የጀመሩት ፋሲሎች በተለይ ከመስመር ተመላላሹ አለምብርሃን ይግዛው ጀርባ እና በከድር ኩሊባሊ መካከል በሚገኘው ቦታ በተደጋጋሚ በሚጣሉ ኳሶች ለጥቃት ሲጋለጡ ተመልክተናል።

በ24ኛው ደቂቃ ላይ ታድያ ወላይታ ድቻዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል ፤ ቃልኪዳን ዘላለም ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ያገኘው በረከት ወልደዮሀንስ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።


በጨዋታው ከግቧ መቆጠር በኃላ ቀስ በቀስ እየተነቃቁ የመጡት ፋሲል ከነማዎች የኳስ ቁጥጥራቸውን ይበልጥ በማሳደግ በተለይ ከግራ መስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል ፤ በአጋማሹም በአንድ አጋጣሚ በረከት ደስታ ከቀኙ የሳጥን ወገን ሰብሮ ገብቶ ወደ ግብ ልኳት ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችበት አጋጣሚ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ከሦስቱ የመሀል ተከላካዮቹ አንዱ የነበረውን ከድር ኩሊባሊን አስወጥተው በምትኩ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስን በማስገባት ወደ ቀደመው አደራደራቸው በመመለስ ነበር የጀመሩት።

ፈጠን ያለ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ፋሲሎች በተለይ በ47ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ እንዲሁም በ51ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላኳቸው አደገኛ ኳሶች ፂሆን መርዕድ በአስገራሚ ብቃት ሊያድንባቸው ችሏል።

የአደራደር ለውጥ ካደረጉ በኃላ ፋሲሎች በተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በዝተው በተለያዩ መንገዶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ድቻዎች በአጋማሹ ይበልጥ ወደ ራሳቸው ሜዳ ተገፍተው ለመከላከል ተገደው ተመልክተናል።


በ60ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ያቀበለውን ኳስ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በግሩም አዟዟር የድቻ ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው መልካሙ ቦጋለን ደርባ ኳሷ ከመረብ በመዋሃዷ ፋሲሎች አቻ መሆን ችለዋል።

ከግቧ በኃላ በተጋጋለ ስሜት በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች አደገኛ እድሎችን መፍጠር የጀመሩበት ነበር በፋሲሎች በኩል በዛብህ መለዮ ከሳጥን ጠርዝ ያደረጋትን ሙከራ ፂሆን ያዳነበት እንዲሁም በአንፃሩ በወላይታ ድቻዎች በኩል ደግሞ ምንይሉ ወንድሙ ያመከነው ግሩም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ እና በሰከንዶች ልዮነት ቃልኪዳን ዘላለም ያደረጋት የመቀስ ምት ሙከራ አደገኞቹ ነበሩ።


ታድያ ተጋግሎ በቀጠለው ጨዋታ ቃልኪዳን ዘላለም ካደረጋት ሙከራ መልስ የጀመረውን የኳስ ሂደት በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ፋሲሎች ሱራፌል ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በረከት ደስታ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ውስጥ በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር ወደ መሪነት መምጣት ችለዋል።

ቀጥለው በነበሩት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በማጥቃቱ ረገድ በተሻለ ፍላጎት ለመጫወት ጥረት ማድረግ ቢጀምሩም ጥራታቸውን የጠበቁ እድሎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ80ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻዎች በማጥቃት ወቅት የሰሩትን የማቀበል ስህተት መነሻ ያደረገውን ሂደት ፋሲሎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በዛብህ መለዮ ያደረሰውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ አስቆጥሮ የፋሲልን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።


ጨዋታው በፋሲል ከተማ የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 37 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ10 ነጥቦች ርቀው 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንፃሩ 34 ነጥብ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በነበሩት 4ኛ ደረጃ ቀጥለዋል።

ያጋሩ