ዛሬ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል አድርገዋል።
በቶማስ ቦጋለ
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3-0 አሸንፏል
አዞዎቹ በአስራ ሁለተኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሜሮን ዘሪሁን እና ድንቅነሽ በቀለ በደራ ጎሣ እና በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብታ አንድ ጨዋታ በተቀጣችው ወርቅነሽ ሜልሜላ ተክተዋል። እንስት ፈረሰኞች በበኩላቸው በአስራ ሁለተኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰፊ የግብ ልዩነት ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ብዙዓየሁ ጸጋዬ በገብርኤላ አበበ ተተክታ ጀምራለች።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን የግብ እድል በመፍጠሩ በኩል ግን አዞዎቹ የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው እንደጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሠረት ወርቅነህ ከ ድንቅነሽ በቀለ የተቀበለችውን ኳስ በማስቆጠር አዞዎቹን መሪ አድርጋለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት የጊዮርጊሷ ቤተልሔም መንተሎ ከቀኝ መስመር ድንቅ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም የላይኛውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅነሽ በቀለ ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ መሠረት ወርቅነህ ብታስቆጥርም እንቅስቃሴዋ ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ተሽሮባታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ ድንቅነሽ በቀለ ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው መሠረት ወርቅነህ ወደግብ ብትሞክርም የጊዮርጊስ ተከላካዮች አውጥተውታል። የጊዮርጊሶቹ ቤተልሔም መንተሎ፣ ዓይናለም እና ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ወደፊት በመጠጋት የግብ እድል ለመፍጠር ቢፈልጉም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። 28ኛው ደቂቃ ላይ ርብቃ ጣሰው ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ ድንቅነሽ በቀለ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር የአዞዎቹን መሪነት አጠናክራለች።
በኳስ ቅብብሉ የተሻሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች ጠንካራ የግብ ሙከራ ማድረግ ሲከብዳቸው ተስተውሏል። 32ኛው ደቂቃ ላይ እቴነሽ ደስታ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት አክርራ መታው ግብ ጠባቂዋ የያዘችውና በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ዓይናለም ዓለማየሁ ከፍቅርአዲስ ገዛኸኝ የተቀበለችውና ከግራ መስመር ወደግብ ሞክራው የላይኛውን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣው ኳስ በጨዋታው የተሻለው ሙከራቸው ነበር። 37ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅነሽ በቀለ በግራ መስመር ሆና ያሻገረችውን ኳስ ነጻ የነበረችው መሠረት ወርቅነህ ዝግጁ ሆና ባለመጠበቋ ትልቅ የግብ እድል አባክናለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ወርቅነሽ መሠለ ከረጅም ርቀት በድንቅ ሁኔታ ብትሞክርም የላይኛው አግዳሚ መልሶባት አዞዎቹን ያስቆጨ አጋጣሚ ሆኗል።
ሁለተኛው አጋማሽ በአንጻሩ ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት ሲሆን 51ኛው ደቂቃ ላይ ትውፊት ካዲዮ ከመሠረት ወርቅነህ የተቀበለችውን ኳስ በማመቻቸት ከሳጥን ውጪ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥራ የአዞዎቹን መሪነት ማሳደግ ችላለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ቤተልሔም መንተሎ ከቀኝ መስመር ጥሩ የግብ ሙከራ ብታደርግም ግብ ጠባቂዋ ይዛዋለች። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር አዞዎቹ ወደኋላ ተመልሶ በመጫወት ጊዮርጊሶች ደግሞ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው በቁጥር በዛ ብለው የተጋጣሚ የግብ ክልል መግባት ሲችሉ የጠራ የግብ እድል በመፍጠሩ በኩል እጅግ ደካማ ነበሩ።
55ኛው ደቂቃ ላይ በአዞዎቹ በኩል ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ድንቅነሽ በቀለ ከቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረችውን ኳስ የላይኛው አግዳሚ መልሶባታል። በጊዮርጊሶች በኩል የተሻለ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቤተልሔም መንተሎ እና ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ኳሱን ወደተጋጣሚ ክልል ይዘው በመግባት የግብ እድል ለመፍጠር ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 82ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ከስንዱ ዳምጠው የተቀበለችውና ወደግብ በግሩም ሁኔታ ሞክራው የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ የጨዋታው የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በአዞዎቹ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
8፡00 ላይ የባህርዳር ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ከፍተኛ ትግል ተደርጎበት ባህር ዳር ከተማ 5-4 አሸንፏል
የጣና ሞገዶቹ በአሥራ ሁለተኛ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ከተለያዩበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው በአሥራ ሁለተኛ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ አቻ ከተለያዩበት ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መስከረም መንግሥቱ ፣ ቅድስት ዘለቀ ፣ ማህደር ባየ እና እታለም አግኑ በ ፍሬወይን ገብሩ ፣ ፀሐይነሽ ጅላ ፣ ረድኤት አስረሳኸኝ እና ብዙኃን እንዳለ ተተክተው ጀምረዋል።
በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የተደረገውና እጀግ አዝናኝ የሆነ ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ እድል በመፍጠሩም በኩል ሀዋሳዎች የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። ሀዋሳዎች በጨዋታው የመጀመሪያ ሰባት (7) ደቂቃዎች አምስት (5) ኢላማውን የጠበቀ አደገኛ ሙከራ ሲያደርጉ ሁለቱ ግብ መሆን ችለዋል። ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነጻነት መና ባስቆጠረችው ግብ መሪ መሆን የቻሉት ሀዋሳዎች ቱሪስት ለማ ከግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ወደግብ ሞክራው ግብጠባቂዋ በያዘችው ኳስ ፣ ሲሣይ ገ/ዋህድ በቀኝ በኩል ከማዕዘን አሻምታው ቅድስት ዘለቀ በግንባሯ ገጭታው ለጥቂት በወጣው ኳስ ፣ ነጻነት መና በግራ መስመር ከምህረት መለሰ የተሻገረላትና ወደግብ ሞክራው ግብጠባቂዋ በያዘችው ኳስ በሚያስገርም ፍጥነት የግብ እድሎችን መፍጠር ሲችሉ 7ኛው ደቂቃ ላይ ነጻነት መና ከሳጥን ውጪ በድንቅ አጨራረስ ለራሷም ለክለቧም ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች። የጣና ሞገዶቹ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 12ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ቤተልሔም ግዛቸው ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ወደግብ ሞክራው የግራውን ቋሚ ተጠግቶ በወጣው ኳስ ነው። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሳባ ኃይለሚካኤል ከምስር ኢብራሂም ተቀብላ ወደግብ የሞከረችውን ኳስ ማህደር ባዬ ጨርፋው በግራ በኩል ወደማዕዘን ወጥቷል።
ሀዋሳ ከተማዎች በተደጋጋሚ በነጻነት መና እና ቱሪስት ለማ የግብ እድል መፍጠር ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ግን ለማስቆጠር አልቻሉም። ከውሃ ረፍት መልስ 28ኛው ደቂቃ ላይ ምስር ኢብራሂም በጥሩ ሁኔታ ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋን አልፋ ለሳባ ኃይለሚካኤል ብታቀብልም ሳባ ወደግብ የሞከረችውን ኳስ የግብጠባቂዋን ቦታ ለመሸፈን የቆመችው ቅድስት ዘለቀ አውጥታዋለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ነጻነት መና ያሻገረችውን ኳስ የ ቃልኪዳን ተስፋየ ጥፋት ተጨምሮበት ነጻ ሆና ያገኘችው ቱሪስት ለማ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝታ ትልቅ የግብ እድል አባክናለች። 41ኛው ደቂቃ ላይ ነጻነት መና በቀኝ መስመር ወደግብ ሞክራው የላዩን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰው ኳስም በሀዋሳዎች በኩል በጣም የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ምስር ኢብራሂም በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ቤዛዊት መንግሥቴ የጣና ሞገዶቹን ተስፋ ያለመለመ ግብ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራለች።
ሁለተኛው አጋማሽ እጅግ በጣም አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በደቂቃዎች ልዩነት የተለያየ ስሜት ሲያስተጋባ የታየበት ሲሆን ከረፍት መልስ የግብ እድል በመፍጠሩም በኳስ ቅብብሉም በኩል የጣና ሞገዶቹ እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 48ኛው ደቂቃ ላይ ሳባ ኃይለሚካኤል ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ ሲመለስ ያገኘችው ሊድያ ጌትነት አስቆጥራ የጣና ሞገዶቹን አቻ ማድረግ ችላለች። 53ኛው ደቂቃ ላይ ሊድያ ጌትነት ወደግብ ሞክራው በሀዋሳ ተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ ምስር ኢብራሂም በግራ እግሯ በግሩም አጨራረስ አስቆጥራ ክለቧ ከመመራት ተነስቶ እንዲመራ አስችላለች።
ከእረፍት መልስ ተቀዛቅዘው የቀረቡት እና የግብ እድል ለመፍጠር የተቸገሩት ሀዋሳዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን መንደሪን ክንድሁን ከቅጣት ምት ወደግብ ሞክራው አዳነች ጌታቸው ስትመልሰው ያገኘችው ሲሳይ ገ/ዋህድ ከሳጥን ውጪ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ሲሳይ ገ/ዋህድ በቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ስታሻግር ነጻ ሆና ያገኘችው ረድኤት አስረሳኸኝ ኃይል ባልነበረው ሙከራ ትልቅ የግብ ማግባት እድል አባክናለች።
ጨዋታው በአስገራሚ ትንቅንቅ ቀጥሎ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሊድያ ጌትነት በግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ለሳባ ኃይለሚካኤል አመቻችታ ስታቀብል ሳባ ኃይለሚካኤል በአስገራሚ አጨራረስ አስቆጥራ የጣና ሞገዶቹን መሪነት ማጠናከር ችላለች። 84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሲሳይ ገ/ዋህድ በቀኝ መስመር ያሻማችውን የማዕዘን ምት ግብ ጠባቂዋ ወደ ውጪ ስታስወጣው በድጋሚ በግራ መስመር ሲሳይ ገ/ዋህድ ስታሻማ ተነካክቶ የተመለሰውን ኳስ ቱሪስት ለማ አስቆጥራ ክለቧን ወደጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርጋለች።
87ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ያገኘችው የባህርዳሯ ምስር ኢብራሂም ብትመታም ግብጠባቂዋ በአስደናቂ ብቃት መልሳዋለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ለሀዋሳ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ዙፋን ደፈርሻ በማስቆጠር ክለቧን አቻ ማድረግ ችላለች።
እጅግ እየተጋጋለ በሄደው የጨዋታ ስሜት ጨዋታው በቻ ውጤት የተጠናቀቀ ቢመስልም መደበኛ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ምስር ኢብራሂም ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ አጨራረስ አስደናቂ ግብ አስቆጥራ የጣና ሞገዶቹ 5-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ አስችላለች።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአቻ መልስ አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል
ኤሌክትሪኮች በ12ኛ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ አንድ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መስከረም ኢሳያስ እና ዕድላዊት ተመስገን በኝቦኝ የን እና ሀብታም እሸቱ ተተክተው ገብተዋል። አዲስ አበባ ከተማዎችም በተመሳሳይ በአርባምንጭ ከተማ 3-2 ከተረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብ ጠባቂዋ ድንቡሽ አባ በስርጉት ተስፋዬ እና ቤተልሔም ሰማኸኝ ደግሞ በዘይነባ ሰይድ ተተክተው ጀምረዋል።
መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የኤሌክትሪኳ ምንትዋብ ዮሐንስ ከግራ መስመር የተሻገረላት እና ኃይል ባልነበረው ሁኔታ በግንባሯ የገጨችው ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ከሳጥን ውጪ በቀኝ መስመር ድንቅ ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች። በሁለት ደቂቃ ልዩነት የአዲስ አበባዋ አርያት ሆዶንግ ከረጅም ርቀት ያገኘችውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ አድናዋለች። በተመሳሳይ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት አርያት በጥሩ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ይዛው የገባችውን ኳስ ወደ ግብ ብትሞክርም አረጋሽ ፀጋ ተደርባ ማስወጣት ችላለች። 17ኛው ደቂቃ ላይ መስከረም ኢሳያስ በቀኝ መስመር ለዙሌይካ ጁሀር ያሻገረችውን ኳስ በግራ መስመር የነበረችው ዙሌይካ ወደ መሀል ገፍታ በመግባት ያደረገችው ሙከራ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል።
24ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር አርያት ሁዶንግ ለቤተልሔም ሰማኸኝ አመቻችታ ብታቀብልም ትልቅ የግብ ማግባት ዕድል የነበራት ቤተልሔም ሰማኸኝም ያገኘችውን ኳስ ከአግዳሚው በላይ በመላክ አባክናለች። ኤሌክትሪኮች በዓይናለም አሳምነው እና ሰላማዊት ንጉሤ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አልነበረም። 40ኛው ደቂቃ ላይ ዘለቃ አሰፋ ኳስ በእጅ በመንካቷ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ የተሰጠውን የቅጣት ምት ትርሲት መገርሣ በግሩም ሁኔታ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ ማድረግ ችላለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በአርያት ኦዶንግ እና ቤተልሔም ሰማኸኝ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት አዲስ አበባዎች ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በአንጻራዊነት ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ኤሌክትሪኮች የተሻሉ ነበሩ። 48ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም አስረሳኸኝ ከግራ መስመር ያገኘችውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥራ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት የአዲስ አበባ ከተማዋ ብሩክታዊት አየለ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በሚያስገርም ፍጥነት በእግሯ በመመለስ ወደማዕዘን ማስወጣት ችላለች። 59ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም አስረሳኸኝ በቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረችው ኳስ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በሄደበት ጨዋታ 75ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ከቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረችው ኳስ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል።
78ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በሻዱ ረጋሳ ዙሌይካ ጁሀር ላይ በሰራችው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቤተልሔም አስረሳኸኝ ስታሻማ ተቀይራ የገባችው ትዝታ ፈጠነ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ማጠናከር ችላለች። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት በግራ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት ቤተልሔም አስረሳኸኝ በግሩም ሁኔታ ስትሞክር ኳሱን መቆጣጠር ያልቻለችው ግብ ጠባቂዋ ዕድለኛ ሆና ኳሱ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቷል። ይሄም በጨዋታው የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።