በመጀመሪያው ትኩረታችን በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች ይነበቡበታል።
👉 አስደማሚው መከላከያ
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከ561 ደቂቃዎች በኋላ ከግብ የታረቀው መከላከያ ከአስገራሚ መሻሻሎች ጋር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ላይ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ ችሏል።
በሊጉ ላለመሸነፍ ቅድሚያ በሰጠ አጨዋወት ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነው መከላከያ ከጥንቃቄ በዘለለ በማጥቃቱ ረገድ ከቢኒያም በላይ ጥረት ባለፈ በውድድር ዘመኑ ይህ ነው የሚባል ፍሬያማ መንገድ ለማሳየት የተቸገረ ቡድን ሆኖ ተመልክተናል።
በ21ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም ግን ባልተለመደ መልኩ ጀብደኝነት የተሞላበትን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። በጨዋታው በተለይ በመጀመርያ አጋማሽ መከላከያዎች ባልተለመደ መልኩ ስድስት እና ከዚያ በላይ ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ ቡና አጋማሽ በማስገባት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ እንዳይመሰርቱ በማድረግ እና ኳሶችን በምቾት እንዳይቀባበሉ በማድረግ ፍፁም የተዋጣለት ምሽትን አሳልፈዋል። በዚህም ሂደት በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ያስቆጠራቸው ግቦች የተገኙት ባሳደሩት ከፍተኛ ጫና መነሻነት በተነጠቁ አልያም ተጋጣሚን በማቀበል ወቅት ስህተት እንዲሰራ በማስገደድ የተገኙ ነበሩ።
በጨዋታው የመከላከያ ተጫዋቾች እንደ ቡድን ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ የነበረ ሲሆን በጫና የማሳደር ሂደት ውስጥ ግን በተለይ ከወገብ በላይ የነበሩት ተጫዋቾች የነበራቸው አስደናቂ የትጋት ደረጃ ፍፁም የተለየ ነበር። ምንም እንኳን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በማጥቃቱ ረገድ ደካማ የሆነውን መከላከያ እየተመለከትን የምንገኝ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ዓይነት በድንገት ሳይጠበቁ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎትን የተመለከትንባቸውን ጥቂት ጨዋታዎች ይታወሳሉ። ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ባህር ዳር እና ወልቂጤን የረቱባቸው እንዲሁም በሀዋሳ በተሸነፉበት ጨዋታ ቡድኑ የተሻለ የማጥቃት ዕቅድን ይዞ አስተውለናል።
መሰል ሂደቶችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስቀጠል የሚኖርበት ጦሩ ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አስቀድሞ በድምሩ በሊጉ በ20 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር የሊጉ ደካማው ማጥቃት ባለቤት ሆኖ ሲቆይ በጥሩ የጨዋታ ዕቅድ ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ያስቆጠራቸው አራት ግቦች በሊጉ በአንድ ጨዋታ ያስቆጠረው ከፍተኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል።
👉 ጅማ አባ ጅፋር ድል አድርጓል
የውድድር ዘመኑን አራተኛ ድል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያስመዘገበው ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡን ወደ 16 በማሳደግ ላለመውረድ በሚያደርገው ጉዞ በተወሰነ መልኩ ተስፋ ፈንጥቋል።
ከሰሞኑ በጨዋታዎች ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነገር ግን ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተቸግሮ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር እርግጥ በተጋጣሚው በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራዎች ረገድ ብልጫ ቢወሰድበትም ከጨዋታው ወሳኙን ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል። በጨዋታው ዳግም በጊዜያዊነት በተሰየሙት የሱፍ ዓሊ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው ጅማ በሁለቱ አጋማሾች ከቆሙ ኳሶች ከተቆጠሩ ግቦች ባህር ዳር ከተማን 2-0 መርታት ችሏል። በሁለተኛ አጋማሽ ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ የተሰነዘረባቸውን ጫና በግብ ጠባቂያቸው ጥረት በማምከን ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ችለዋል።
ነጥቡን 16 በማድረስ ተስፋ የፈነጠቀው የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባ ጅፋር በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመግጠሙ አስቀድሞ ከአርባምንጭ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ጋር እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ከፊቱ ይጠብቁታል። በመሆኑም ይህንን የአሸናፊነት ስሜት በማስቀጠል ካለበት አደጋ ተመንጥቆ ይወጣ ይሆነ ወይ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 አዳማ ከተማ ሌላኛው ከተማውን ያልተጠቀመ ቡድን ሆኗል
የሊጉ ውድድር በአዳማ ከተማ በነበረው የስድስት የጨዋታ ሳምንታት ቆይታ በደጋፊያቸው ፊት የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች ማሳካት የቻሉት አምስት ነጥብ ብቻ ሆኗል።
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ምንም እንኳን በከተማቸው የሚጫወቱ ቡድኖች እንደ አጠቃላይ ለከተማውም ሆነ ለሜዳው እንግዳ የመሆናቸው ነገር ከግምት ውስጥ ቢገባም በተሻለ ቁጥር በበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ታጅበው ጨዋታ እንደማድረጋቸው የተሻለ ውጤት ይይዛሉ የሚል ጥበቃ መኖሩ አይቀሬ ነው። አዳማ ከተማም እርግጥ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች መጠነኛ የቁጥር መቀነስ ተመለከትን እንጂ ጨዋታዎቹን እጅግ በርካታ ቁጥር ባለው የክለቡ ደጋፊ ታጅቦ አድርጓል።
በእነዚሁ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች 5 (31.25%) ብቻ ያሳካ ሲሆን ይህም አምና በሊጉ በከተማቸው ውድድር ያደረጉ ቡድኖች ከነበራቸው 57.73% የነጥብ ማሳካት ንፃሬ እንዲሁም ዘንድሮ እስከ አዳማው ውድድር ድረስ በከተማቸው የተጫወቱ ቡድኖች ካስመዘገቡት 41.98% ንፃሬ አንፃር እጅግ ደካማ የሚባል ነው። በሊጉ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች አቻ በመለያየት የሚመራው ቡድኑ ይህን ሂደት ለመቀልበስ በተለይ ደጋፊዎቹን በሚገባ ይጠቀማል ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ሳይሆን ቀርቷል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአሁኑ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ይመራ የነበረው ባህርዳር ከተማ በመቀመጫ ከተማው በተደረጉ የአምስት የጨዋታ ሳምንታት ማግኘት ከሚገባው ነጥብ 83.34% በማሳካት በሊጉ የተሻለው ቡድን ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በሜዳው 8.4% ብቻ ነጥቦችን በማሳካት ዝቅተኛው ቡድን እንደሆኑ አይዘነጋም።
👉 ድሬዳዋ እያንሰራራ ይገኛል
ድሬዳዋ ከተማ በጨዋታ ሳምንቱ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ትልቅ ዋጋ በነበረው ጨዋታ በሊጉ ግርጌ ይገኝ የነበረው ሰበታ ከተማን በመርታት ነጥቡን 24 አድርሷል።
ከሁለተኛው ዙር ወዲህ በአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ እየተመራ የሚገኘው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ በጨዋታዎች አስቀድሞ ግብ በማስቆጠር ያገኘውን መሪነት አስጠብቆ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህን ሂደት በተለይ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ አስቀድመው ያስቆጠሩትን ግብ ለማስጠበቅ ይበልጥ ወደ ኋላ ተስበው በመጫወታቸው ተደጋጋሚ ጫናዎችን ራሳቸው ላይ የገበዙት ድሬዎች በመጨረሻ ግብ አስተናግደው አቻ ሲለያዩ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም እንዲሁ አስቀድመው በአቤል አሰበ አማካኝነት ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል። ምንም እንኳን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በኋላ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው አሸንፈው መውጣት ቢችሉም ሰበታ ከተማዎች በተደጋጋሚ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ሳጥናቸውን ሲጎበኙ አምሽተዋል።
አሰልጣኙ ከጨዋታ በኋላም እንደተናገሩት ካሉበት ቀጠና ለመውጣት ያገኟትን ነገር የማስጠበቅ ዝንባሌ እንዳለ ያመኑ ሲሆን ይህም ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከስጋት መላቀቅ ሲችሉ መቀረፍ የሚችል እንደሆነ ጠቁመዋል። በሁለተኛው ዙር ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ቡድኑ አሁን ላይ ነጥቡን 24 ያደረሰ ሲሆን በቀጣይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ከቻለ በሰንጠረዡ ካለው የቡድኖች የነጥብ መቀራረብ የተነሳ በፍጥነት እስከ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ሊልበት የሚችለውን ዕድል መፍጠር ይችላል።
👉 የሀዲያ ሆሳዕና ወደ መሀል የተጠጋ የተከላካይ መስመር
በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትናቸው ጨዋታዎች መካከል እጅግ አዝናኝ የነበረው እና ስድስት ግቦች የተቆጠሩበት የአዲስ አበባ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። በጨዋታው ታድያ በተለይ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የተቆጠሩት ግቦች ትኩረት የሚስቡ ናቸው።
በጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕናዎች የመጨረሻ የመከላከል መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ በተጠጋጋ አቋቋም እንዲከላከሉ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። በዚህ ሂደት ግን ሦስቱም ግቦች ሲቆጠሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ከሀዲያ ሆሳዕና ተከላካዮች ጀርባ የነበረውን ሜዳ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በመጠቀም የተገኙ ነበሩ።
ወደ መሀል ተጠግቶ መጫወት ጥሩ የቡድን ሥራን የሚጠይቅ ጨዋታ ሲሆን በዚህም የመጫወቻ ሜዳውን በማጥበብ ጨዋታውን ለተጋጣሚ የማይመች ለማድረግ ይረዳል። ይህ አጨዋወት እንደ ቡድን መጫወትን የሚጠይቅ ነው። ይህም ማለት በመሰረታዊነት ቡድኑ በተለይም የኋለኛው የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች እንደ ቡድን ተናበው ከፍ ዝቅ ማለት እንዲሁም ከፊት ያሉት ተጫዋቾች ደግሞ በተቀናጀ መልኩ ጫና አሳድረው ኳሱን መንጠቅ ካልቻሉ አጨዋወቱ ከፍተኛ ስጋት እና ከፍተኛ ምላሽ ያለው እንደመሆኑ አተገባበር ላይ የሚሰሩ ስህተቶች ካሉ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀሬ ነው።
ሆሳዕና ላይ በተቆጠሩት ሥስቱም ግቦች ላይ ከላይ የጠቀስናቸው መሰረታዊ እሳቤዎች በአግባቡ መተግበር ባለመቻላቸው ቡድኑ በዚህ አደገኛ አጨዋወት ግቦችን ለማስተናገድ ተገዷል። ምንም እንኳን ጨዋታው በአቻ ውጤት ቢጠናቀቅም ሀዲያ ሆሳዕና በቀጣይ በዚህ መንገድ ለመጫወት የሚያስብ ከሆነ በጣም ተሻሽሎ መቅረብ እንዳለበት ግን የጠቆመ ነበር።