ኢትዮጵያዊው ዳኛ የቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን ይመራል

የፊታችን ቅዳሜ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ የሚደረገው የአል-አህሊ እና ኢኤስ ሴቲፍ የቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን ኢትዮጵያዊው የመሀል ዳኛ ይመሩታል፡፡

በካፍ የክለቦች እግር ኳስ ውድድር ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ መደረጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በ2022 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ መርሀግብሮች መካከል በግብፁ አል-አህሊ እና በአልጄሪያው ክለብ ኢኤስ ሴቲፍ መካከል የፊታችን ቅዳሜ ሚያዝያ 30 አመሻሽ 10፡00 ሰዓት ሲል በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በሚገኘው አል-ሰላም ስታዲየም የሚከወነውን ይህን ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ሱዳናዊው መሀመድ አብደላ እና ቻዳዊው ኢሳ ያያ በረዳትነት ቦትስዋናዊው ጆሾ ቦንዶ በአንፃሩ በአራተኛ ዳኝነት ከባምላክ ጋር ተመድበዋል፡፡

በዚህ የቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የቫር ዳኝነት የሚተገበር ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫው በሙቀታማ አየር ጨዋታ ሳይጠናቀቅ የፈፀሙት ዛምቢያዊው አወዛጋቢ ጃኒ ሲካንዜ ይህን የቫር ዳኝነት ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር ለመምራት ተሰይመዋል፡፡