የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ተጠናቋል

በቶማስ ቦጋለ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች አንደኛውን ዙር አገባዷል።

መከላከያ በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል

ረፋድ 3፡00 ላይ የመከላከያ እና የጌዴኦ ዲላ ጨዋታ ሲደረግ በአስራ ሁለተኛ ሳምንት አራፊ የነበሩት መከላከያዎች በቀደመው ሳምንት አቃቂ ቃሊቲን በሰፊ የግብ ልዩነት ከረቱበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ መዓድን ሣህሉ በዙሪያሽወርቅ መልኬ ተተክታለች። ጌዴኦ ዲላዎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሳምንት አቃቂ ቃሊቲን 2-1 ከረቱበት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ሣራ ብርሃኑ በመኪያ ከድር ፣ ጽዮን ማንጁራ እና ኃይማኖት ግርማ ደግሞ በአልማዝ ብርሃኔ እና ጤናዬ ወመሴ ተለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀዝቃዛ እና ዳመናማ ሆኖ ለጨዋታ ምቹ በነበረ የአየር ሁኔታ መደረግ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የመከላከያ ፍጹም የበላይነት የታየበት ሲሆን 8ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ባሻማችው ኳስ ቤዛዊት ተስፋየ የግብ እድል ስትፈጥርበት ኳሱን በአየር ላይ ያገኘችው ሥራ ይርዳው በግሩም ሁኔታ (ተገልብጣ) ወደግብ ስትሞክር ኳሱን ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራ መከላከያን መሪ ማድረግ ችላለች።

18ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ በቀኝ መስመር ላለችው ሥራ ይርዳው አመቻችታ ስታቀብል ወደግብ የመሞከርም የማቀበልም አማራጭ ያገኘችው ሥራ ለገነት ኃይሉ ስታቀብል ገነት ወደግብ የሞከረችው ኳስ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት የተቸገሩት ጌዴኦ ዲላዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በግራ መስመር መቅደስ ማሞ አዲስ ንጉሤ ላይ በሠራችው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ራሷ አዲስ ንጉሤ ወደግብ ብትሞክርም ግብጠባቂዋ በቀላሉ ይዛዋለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት መሳይ ተመስገን በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን እና ትልቅ የግብ እድል የፈጠረውን ኳስ የጌዴኦ ዲላዋ ኃይማኖት ግርማ በሚያስገርም ፍጥነት በግንባሯ ገጭታ ማስወጣት ችላለች። 29ኛው ደቂቃ ላይ ዝናቧ ሽፈራው ሴናፍ ዋቁማ ላይ በሠራችው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሴናፍ በግሩም ሁኔታ ወደግብ ሞክራው ኳሱ የግብጠባቂዋን እጅ ጥሶ ገብቷል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት መሳይ ተመስገን በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ መቅደስ ማሞ በግንባሯ ስትገጭ ለመመለስ የሞከረችው እና እድለኛ ያልነበረችው ጽዮን ማንጁራ በራሷ ላይ ልታስቆጥር ችላለች። በተመሳሳይ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻለችው ሥራ ይርዳው በቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ መሳይ ተመስገን በግሩም ሁኔታ በግንባሯ ስትገጭ የግራውን ቋሚ ነክቶ ሊገባ ችሏል።

መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል መግባት እና የግብ እድል መፍጠር ሲችሉ በአንጻሩ ጌዴኦ ዲላዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት በጣም ሲቸገሩ ታይቷል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ በጥሩ ሁኔታ ገፍታ በወሰደችው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ስትገናኝ በግራ መስመር ላይ ላለችው መሳይ ተመስገን የማቀበል አማራጭ ቢኖራትም በራሷ ሞክራው ግብጠባዊዋ ይዛባት ትልቅ የግብ ማግባት እድል አባክናለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ መዓድን ሣህሉ በቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ልትቆጣጠረው ባትችልም በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ገብታ ኳሱን የያዘችው መሳይ ተመስገን የግብ ሙከራ ብታደርግም ግብጠባቂዋ በሚያስደንቅ ብቃት መልሳዋለች።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ጌዴኦ ዲላዎች በኳስ ቁጥጥሩም የግብ እድል በመፍጠሩም በኩል የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ጡባ ነሥሮ በቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ አዲስ ንጉሤ በግንባሯ ለመግጨት ስትሞክር ተጨርፎ የወጣባት ቢመስልም ሳጥኑ ውስጥ በግራ በኩል ከአዲስ ጀርባ ሆና ኳሱን ያገኘችው ይታገሱ ተገኝወርቅ በምርጥ አጨራረስ አስቆጥራ ክለቧን ወደጨዋታው ለመመለስ ሞክራለች። መከላከያዎች በመዳከማቸው ምክንያት ወደኋላ ተስበው ለመጫወት ሲገደዱ ጌዴኦ ዲላዎች በበኩላቸው በፍጥነት ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ተጭነው መጫወት እና ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ይታገሱ ተገኝወርቅ ሳጥን ውስጥ በቀኝ መስመር ለነበረችውና ተቀይራ ገብታ ጥሩ እንቅስቃሴ ላሳየችው ጡባ ነሥሮ አመቻችታ ስታቀብል ግብ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ጡባ ነሥሮ የሞከረችውን ኳስ ግብጠባቂዋ በሚያስገርም ብቃት መልሳዋለች።

64ኛው ደቂቃ ላይ ማርያም ታደሰ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻማችውን ኳስ ተጠቅማ ቤተል ጢባ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም በድጋሚ ግብ ጠባቂዋ በሚያስገርም ፍጥነት መልሳዋለች። ከውሀ እረፍት መልስ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ መከላከያዎች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 85ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው ወደግብ ሊቀይሩት ችለዋል። ጎሉንም ከመዓድን ሣህሉ ከረጅም ርቀት ተሰንጥቆ የደረሳትን ኳስ ወደቀኙ የሜዳ ክፍል ባጋደለ ቦታ ላይ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ እርጋታ በተሞላበት ምርጥ አጨራረስ በማስቆጠር ሐት-ሪክ መሥራት ችላለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ሴናፍ ዋቁማ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ለማስቆጠር ትክክለኛ ቦታ የያዘችው ተቀይራ የገባችው ረሂማ ዘርጋው በአግባቡ ተጠቅማ በማስቆጠር ጨዋታው በመከላከያ 6-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ እና ድሬደዋ ነጥብ ተጋርተዋል

8፡00 ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ ሲገናኙ ድሬዎች በ12ኛ ሳምንት በቦሌ ክፍለከተማ 4-2 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ባንቺይርጋ ተስፋየ ፣ ትዕግሥት ዳዊት እና አሥራት ዓለሙ በ ሕይወት ዳንኤል ፣ ፀሐይ ሂፋሞ እና ሰርካለም ባሳ ተተክተው ጀምረዋል። አዳማዎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ ሰርካዲስ ጉታ በትዕግሥት ዘውዴ ተተክታ ወደ ሜዳ ገብታለች።

በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ በተደረገው እና አዝናኝ እንዲሁም ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የተሻለ የግብ እድል በመፍጠሩም በኩል ድሬዎች የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። ጨዋታው እንደጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ሔለን እሸቱ ኢላማውን ባለመጠበቋ እና ኳሱ የግራውን ቋሚ ተጠግቶ በመውጣቱ አዳማዎችን መሪ ሊያደርግ የሚችል ትልቅ እድል አባክናለች። 8ኛው ደቂቃ ላይ ግን ድሬዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግቡንም ከረጅም ርቀት በተደጋጋሚ እያስቆጠረች የምትገኘው ቤተልሔም ታምሩ ዛሬም በተመሳሳይ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት አግኝታ በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠር ችላለች።

18ኛው ደቂቃ ላይ ዮዲት መኮንን እና ሰርካዲስ ጉታ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ መጨረሻ ላይ ሰርካዲስ ጉታ ግብጠባቂዋን አልፋ ወደግራ መስመር ገፍታ ወደግብ ስትሞክር የድሬዋ ቤዛዊት ንጉሤ ራሷን ለአደጋ አጋልጣ ግብ የሚሆን ኳስ በድንቅ ፍጥነት አድና ከግቡ የግራ ቋሚ ጋር ተጋጭታ ጉዳት አስተናግዳለች። 30ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ ከረጅም ርቀት በሚያስገርም ኃይል ለራሷም ለክለቧም ሁለተኛ ግብ አስቆጥራ የድሬን መሪነት አጠናክራለች። አዳማዎች ኳሱን የተሻለ በመቀባበል በተደጋጋሚ በምርቃት ፈለቀ የተለያዩ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። 34ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዋ አሥራት ዓለሙ ከሰናይት ባሩዳ የተሻገረላትን ኳስ የግብጠባቂዋን መውጣት ተመልክታ በዐየር ላይ (ቺፕ) ብትሞክርም የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ምርቃት ፈለቀ ከግራ መስመር ወደ ግብ ያሻማችውና ትልቅ የግብ እድል ሊፈጥር የሚችለውን ኳስ የድሬዋ ገነት ፈረደ በፍጥነት በግንባሯ በመግጨት ማስወጣት ችላለች።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ሰናይት ባሩዳ ሔለን እሸቱ ላይ የሠራችውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ከቆሙ ኳሶች ብዙ የግብ እድሎችን እየፈጠረች ያለችውና ከመጀመሪያዎቹ ሳምንቶች ትሰለፍበት ከነበረው የመሀል የተከላካይ ቦታ በተለየ መልኩ በአማካይ እየተሰለፈች የግብ እድሎችን የመፍጠር ኃላፊነት የተሰጣት መሠሉ አበራ በሚያስገርም ብቃት ወደግብ ስትሞክረው የግብጠባቂዋን እጅ ጥሶ መግባት ችሏል። ይሄም የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኗል።

ሁለተኛው አጋማሽም ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ 55ኛው ደቂቃ ላይ ታይቷል። በተጠቀሰው ደቂቃም የአዳማዋ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ወደግብ ስታሻማ በግንባሯ ገጭታ የማስቆጠር አጋጣሚ ያገኘችው ሰርካዲስ ጉታ ኳሱን ሳታገኘው በመቅረቷ የግብ እድሉ ባክኗል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሰርካለም ባሳ አመቻችታ ባቀበለቻት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር መገናኘት የቻለችው ታደለች አብርሃም ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ይዛዋለች። ይሄም ድሬዎችን ያስቆጨ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። 62ኛው ደቂቃ ላይ ጽዮን ፈየራ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ደግሞ ቤተልሔም ታምሩ አስቆጥራ ሐት-ሪክ መሥራት ችላለች።

67ኛው ደቂቃ ላይ ባንቺይርጋ ተስፋየን በሁለት ቢጫ ያጡትና በቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች ከጨዋታው ቅኝት ያስወጣቸው አጋጣሚ ሆኖባቸዋል። የተሻለውን የመጨረሻ ሙከራ ያደረጉትም 68ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ቤተልሔም ታምሩ በግራ መስመር ያገኘችውን የቅጣት ምት ኳስ ወደግብ ብትሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። 71ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ በግሩም ሁኔታ በቀኝ መስመር ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ለሔለን እሸቱ አመቻችታ ስታቀብል ሔለንም ከሳጥን ውጪ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥራ አዳማዎችን ወደጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርጋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ድሬዎች ውጤት ለማስጠበቅ ወደኋላ ተስበው መጫወት ሲጀምሩ አዳማዎች ያላቸውን የማጥቃት አማራጭ ሁሉ እየቀያየሩ መሞከር ቀጥለዋል።

80ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር መሰሉ አበራ ከቅጣት ምት ወደግብ ስትሞክር የድሬዋ ተከላካይ ዘቢብ ኃይለሥላሴ በግንባሯ በመግጨት የማዕዘን ምት ማድረግ ችላለች። 83ኛው ደቂቃ ላይ ሰብለ ቶጋ ከረጅም ርቀት ያገኘችውን የቅጣት ምት ወደግብ ስታሻማ ተቀይራ የገባችው ትዕግሥት ዘውዴ ለግቡ ጀርባዋን ሰጥታ ቆማ የነበረ ቢሆንም በአስገራሚ ሁኔታ ኳሱን ወደኋላ በመግጨት አስቆጥራዋለች። 88ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ በቀላሉ ወደግብ መሞከር ብትችልም ተገልብጣ (በፎርቢች) ለመሞከር የፈለገችው ሄለን እሸቱ በመዘግየቷ ኳሱን ልታገኘው አልቻለችም። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በተመሳሳይ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ መሰሉ አበራ በአስደናቂ ሁኔታ ወደግብ ብትሞክርም የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። ጨዋታውም 3-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


ቦሌ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር በድል ደምድሟል

10፡00 ላይ የ13ኛ ሳምንት እና የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻው ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ እና በቦሌ ክፍለከተማ መካከል ሲደረግ ከሁለት ቀናት በፊት ከአሰልጣኛቸው ዮናስ ወርቁ ጋር የተለያዩት አቃቂዎች በ12 ሳምንት በጌዴኦ ዲላ 2-1 ከተረቱበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲቀርቡ ቦሌዎች በበኩላቸው በዛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 4-2 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሒሩት ብርሃኑ እና ስንታየሁ ኢርኮ በሒሩት ተስፋዬ እና ሜላት ጌታቸው ተተክተው ጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር እና ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቦሌዎች 2ኛው ደቂቃ ላይ ምርጥነሸ ዮሐንስ በቀኝ መስመር ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ምርጥነሽ ዮሐንስ በቀኝ መስመር ለንግሥት በቀለ አመቻችታ ስታቀብል ንግሥት በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ኢላማውን ግን መጠበቅ አልቻለችም። ቦሌዎች በሲፈን ተስፋዬ አቃቂዎች በሄለን አባተ እና ወለላ ባልቻ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አልነበረም። 19ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግሥት ሽኩር ምርጥነሽ ዮሐንስ ላይ በሠራችው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ንግሥት በቀለ አስቆጥራ ቦሌዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። 23ኛው ደቂቃ ላይ ምርጥነሽ ዮሐንስ የአቃቂ ተከላካዮች ስህተት ተጨምሮበት ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ ጨርፋ ወደ ማዕዘን አስወጥታዋለች።

በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የሆኑት የመጨረሻ ኳስ ላይ ግን ውጤታማ መሆን የከበዳቸው አቃቂዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ወለላ ባልቻ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት አክርራ መታው ግብጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ሀና ቱርጋ ኳሱን በትክክል ባለማግኘቷ ተጨርፎ ሲወጣባት ቡድኗን አቻ ማድረግ የሚችል ትልቅ ዕድል አባክናለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሲፈን ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ንግሥት በቀለ ኳሱን ስትገፋ በመዘግየቷ እና የግቡን አንግል እያጠበበች ሄዳ በቀኝ መስመር ወደ ግብ ስትሞክር ግብ ጠባቂዋ ወደ ማዕዘን አስወጥተዋለች ፤ ይሄም ቦሌዎችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት አቃቂዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም መኮንን ከሄለን አባተ ተቀብላ ወደ ግብ የሞከረችውንና ፍሬህይወት በድሉ ከበሬዱ በቀለ ተቀብላ ከረጅም ርቀት ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የያዘቻችው ኳሶች በአቃቂ በኩል የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን በሁለቱም በኩል የተሻለ ፉከክር የታየበት ሲሆን 54ኛው ደቂቃ ላይ ከወትሮው በተለየ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገችውና ብዙ የግብ ዕድሎችን ያባከነችው ንግሥት በቀለ በግራ መስመር እየገፋች ወደ ሳጥን ይዛው በገባችው ኳስ ግብጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ብትገናኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ከግብ ጠባቂ ጋር መገናኘት የቻለችው ንግሥት በቀለ ትልቅ ግብ የማግባት አጋጣሚ ስታባክን ቦሌዎችን በጣም ያስቆጨ ሌላው አጋጣሚ ነበር። 63ኛው ደቂቃ ላይ በአቃቂ በኩል በየጨዋታዎቹ አስደናቂ እንቅስቃሴ የምታደርገው ፣ በተመልካቾች ለመታየት ከሚናፈቁ እና ከፍተኛ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው ዓይናለም መኮንን በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ወደግብ በግሩም ሁኔታ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ በላይ በኩል ወደማዕዘን እንዲወጣ ስታደርግ አቃቂዎችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።

ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በሄደው የጨዋታ ስሜት 81ኛው ደቂቃ ላይ ምርጥነሽ ዮሐንስ ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ ያገኘችው ንግሥት በቀለ ወደ ግብ ብትሞክርም ግብጠባቂዋ በፍጥነት አድናዋለች። 85ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ስትፈጥር የነበረችው ምርጥነሽ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ሆና ወደ ተጋጣሚ ክልል እየተጠጋች በነበረበት ሁኔታ የግቡን አንግል ለማጥበብ ከወጣችው ግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ በድንቅ አጨራረስ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ማጠናከር ችላለች። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ መዐዛ አብደላ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ የአቃቂ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ናት በሚል መዘናጋት ተጨምሮበት ያገኘችው ተቀይራ የገባችው ሜላት ጌታቸው ከግራ መስመር ወደ መሀል ገፍታ በማመቻቸት በተረጋጋ ሁኔታ በመጨረስ ለቡድኗ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችላለች። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የቅጣት ምት ያገኘችው ዓይናለም መኮንን አቃቂን ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ ስታስቆጥር በአስደናቂ ብቃት ወደ ግብ የሞከረችው ኳስ የግብ ጠባቂዋን እጅ ጥሶ ገብቷል። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በቦሌ ክፍለከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።