የዓለም ዋንጫ ወደ ሀገራችን ሊመጣ መሆኑን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው የዓለማችን የትልቁ ውድድር ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ መሆኑን አስመልክቶ ኮካ ኮላ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በህዳር ወር በኳታር አስተናጋጅነት የሚካሄደው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ውድድር ከመከወኑ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዋንጫ አስጎብኚነት ከተመረጡ ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። የውድድሩ ይፋዊ አጋር የሆነው ኮካ ኮላ የሀገራችን የእግር ኳስ ቤተሰቦች ዋንጫውን በቅርበት እንዲመለከቱት በአህጉራችን አፍሪካ ከተመረጡ ዘጠኝ ሀገራት (አምስቱ ወደ ዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት መሆናቸው ልብ ይሏል) መካከል አንዷ አድርጎ ዋንጫውን ግንቦት 16 እና 17 በአዲስ አበባ እንዲቆይ ያደርጋል። ይህንን አስመልክቶም ረፋድ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የኮካ ኮላ ሲኒየር ፍራንቻይዝ ማናጀር በኢትዮጵያ እና ምስራቅ አፍሪካ አቶ ዓለም አለማየሁ፣ የኮካ ኮላ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዳረን ዊልሰን፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል። በቅድሚያም አቶ ዓለም አለማየሁ “ያለፉትን 136 ዓመታት የስፖርት ቤተሰቡን ለማስደሰት ሰርተናል። በሀገራችን ኢትዮጵያም የተለያዩ ስራዎችን ሰርተናል። የ2022 የዓለም ዋንጫ ከመደረጉ በፊት ፊፋ እና የውድድሩ አጋር ኮካ ኮላ ተነጋግረን ዋንጫውን በየሀገሩ ለማዞር አስበናል። የዓለም ዋንጫውን በሀገራችን ከዚህ ቀደም ለ2 ጊዜ አምጥተናል። ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫውን እናመጣለን። በዚህም ደግሞ ደስተኞች ነን” የሚል መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ዋንጫው ግንቦት 16 እና 17 አዲስ አበባ ሲቆይ ከ12 ሺ በላይ ሰው ዋንጫውን የማየት ዕድል እንደሚያገኝ አመላክተዋል።

ከተጋባዥ እንግዶች ውጪ ዋንጫውን ማየት እና ታሪካዊ ምስል ማስቀረት የሚፈልግ ሰው በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት 10 ባለ500 ሚሊ ሊትር የኮካ ኮላ የፕላስቲክ ጠርሙስ ላይ ያለውን ልጣጭ ልጦ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ይዞ በመሄድ ትኬት መውሰድ እንደሚችል ተገልጿል።

6.142 ኪሎ ግራም የሚመዝነው እና ውድድሩን ያሸነፉ የቡድን አባላት እንዲሁም የሀገር ርዕሰ-ብሔሮች ብቻ በእጃቸው የሚነኩትን ዋንጫ ወደ ሀገራችን ይዞ የሚመጣው ታዋቂው የቀድሞ ተጫዋች ደግሞ ፈረንሳዊው ዴቪድ ትሬዝጌት እንደሆነ የኮካ ኮላ ማኔጂንግ ዳይሬክተ ሚስተር ዳረን ዊልሰን ተናግረዋል። ግለሰቡ ጨምረው ወደ ሀገራችን የሚመጣውን ተጋባዥ እንግዳ በገለፁበት ንግግራቸው ኮካ ኮላን በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።

“የዓለም ትልቁን ውድድር ትክክለኛውን ዋንጫ በማምጣታችን በጣም ደስተኞች ነን። ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ 62 ዓመታት ሆኖታል እየሰራ ካለ። ስንጀምር በአንድ ፋብሪካ ነበር። አሁን 5ኛ ፋብሪካችንን ገንብተናል። በምርት ሰርጭቱ ሂደት ከ70 ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድሉ ላይ ተሳታፊ ናቸው። ከዋናው ዋንጫ ጋርም የስፖርት ቤተሰቡ ትዝታ እንዲያስቀር እናደርጋለን።” ብለዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 9 ሀገራት ለዛውም ካለፉት 5 ሀገራት ውጪ ካሉት ውስጥ አንዱ መሆኗ ትልቅ ነገር ነው።” ካሉ በኋላ “ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት መለወጥ አለብን።” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈው ዋንጫው ሀገራችን እንዲመጣ ላደረጉ የኮካ ኮላ ሀላፊዎች በፌዴሬሽኑ ስም ምስጋና ሲያቀርቡ ተደምጧል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትም ዋንጫው መምጣቱ ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር የተናገሩ ሲሆን በመሐል መሐል የኮካ ኮላን ኳስ የሚያሸልሙ አዝናኝ ጥያቄዎች ተከናውነው በጋራ የፎቶ የመነሳት መርሐ-ግብር መግለጫው ፍፃሜውን አግኝቷል።