የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

ሦስተኛው ፅሁፋችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ አሰልጣኞች ላይ ይሆናል።

👉 የሱፍ ዓሊ ዳግም ጅማን ተረክቧል

ከቀናት በፊት ዋና አሰልጣኛቸው አሸናፊ በቀለን ያገዱት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በየሱፍ ዓሊ እየተመሩ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ በድል ተወጥተዋል።

ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩት አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም ቡድኑ በ2011 የውድድር ዘመን ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ባልነበረባቸው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች በጊዜያዊነት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መምራቱ ሲታወስ በሊጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች የዋና አሰልጣኞች አለመኖሩን ተከትሎ ቡድኑን ተረክቦ ሲመራ ቆይቷል።

አሁን ደግሞ በአሰልጣኝ አሸናፊ ምትክ ቡድኑን በመራበት የመጀመሪያ ጨዋታ ድል ማስመዝገብ ችሏል። በጨዋታው ቢጫ ካርድ የተመለከተው አሰልጣኙ በሜዳው ጠርዝ በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆኖ እየተቁነጠነጠ ቡድኑን ሲመራ ተመልክተናል። የመውረድ ስጋት የተደቀነበት ቡድኑ በየሱፍ የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፉ በበጎነት የሚነሳ ሲሆን ይህን የተነሳሽነት ስሜት በማስቀጠል ምን ያህል ይጓዛሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በውጤት መጥፋት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች አሰልጣኝ አሸናፊን ያገደው ጅማ ከወራት በፊት ደግሞ በአሰልጣኙ ምርጫ ወደ ጅማ የመጡት እና ምክትላቸው የነበሩት እያሱ መርሃፅድቅን እንዲሁ ማገዱ አይዘነጋም።

👉 ዮሐንስ ሳህሌን የተከታው ዮርዳኖስ ዓባይ

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከጫና መነሻነት በተፈጠረ የጤና እክል ምክንያትነት መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ ተገኝተው መምራት ባልቻሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምትክ ረዳታቸው የሆነው ዮርዳኖስ ዓባይ ጨዋታውን መርቷል።

በ1990ዎቹ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ አንፀባርቀው ከወጡ ኮከቦች አንዱ የነበረው ዮርዳኖስ እግርኳስን ካቆመ ወዲህ ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ በመከላከያ የዮሐንስ ሳህሌ ረዳት በመሆን ወደ ሥልጠናው እየገባ ይገኛል።

ለወትሮውም ቢሆን አሰልጣኝ ዮሐንስ በጨዋታዎች ወቅት እምብዛም ከወንበራቸው ተነስተው ጨዋታዎችን ሲመሩ አለመልከታችንን ተከትሎ ቡድኑን በጨዋታ ወቅት የመምራቱ ድርሻ የዮርዳኖስ ኃላፊነት እንደነበር አይዘነጋም። ታድያ ይህም ልምድ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ሳያግዘው አልቀረም።

በአደራ ቡድኑን በመራበት ጨዋታ ጦሩ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ከተለየ የጨዋታ ዕቅድ ጋር አራት ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፉ ገና ወደ ሥልጠናው ሀዲድ እየገባ ለሚገኘው ዮርዳኖስ ዓባይ የማይረሳ ቀን ያደርገዋል።

👉 የብርሃን ደበሌ ቅያሬዎች

ሰበታ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች መካከል በሰበታ ከተማ በኩል በ47ኛው ደቂቃ የተደረጉት ቅያሬዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረባቸው ግብ እየተመሩ ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ሰበታ ከተማ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ብርሃን ደበሌ በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በ47ኛው ደቂቃ አስወጥተው በምትካቸው ዘላለም ኢሳያስ እና ቢስማርክ አፒያን አስገብተዋል።

ሆኖም ቅያሪዎቹ እንደታሰው የቡድኑን ማጥቃት በማሻሻል ውጤት ከማስገኘት ይልቅ የማጥቃት ሚዛኑን ያፋለሱ ቅያሬዎች እንደነበሩ የታዘብን ሲሆን በዚህም ሰበታ በተለይ ከመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች በዘለለ አማራጭ እንዳይኖረው ያስገደደ አጋጣሚን ፈጥሯል። ከዚህ ቀደምም በነበረው ሂደት በተመሳሳይ በቡድኑ ማጥቃት ላይ በተሻለ በጎ ተፅዕኖ የነበራቸው ተጫዋቾች ከሜዳ ተቀይረው ሲወጡ ታዝበናል። ይህም ቡድኑ ተጨማሪ የማጥቂያ መንገዶችን አግኝቶ የተጋጣሚውን በር ደጋግሞ ከማንኳኳት ይልቅ የግብ ዕድል መፍጠሪያ መላዎቹ ተዳክመው አጋጣሚዎችን መፍጠር እንዲሳነው ሲያደርግ ይታያል።

አሰልጣኞች ከሚመዘኑባቸው መመዘኛዎች አንዱ የጨዋታ ወቅት አስተዳደር እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ጨዋታን በማንበብ የሚደረጉ ግለሰባዊም ሆነ የስልት ለውጦች ተጠቃሾች ናቸው። ሰበታ ከተማም ከተጋረጠበት የመውረድ አደጋ አንፃር በዚህ ረገድ እጅግ ስኬታማ የሆኑ ቅያሪዎችን ይፈልጋል።

👉 የኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ መንገድ እና የተጫዋቾች ጥራት

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድኑ በመከላከያ 4-0 ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው አስተያየት ስለተጫዋቾች የጥራት ጉዳይ ባልተለመደ መልኩ ሀሳብ ሲሰነዝር አድምጠናል።

በአጨዋወታቸው ላይ ስለሚታዩ ክፍተቶች የተጠየቀው አሰልጣኙ ተከታዩን ብሏል ፤

“የተጫዋች ጥራት ይጠይቃል፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም ግን አጠቃላይ ዛሬ 4-0 ተሸንፈናል፡፡ ይሄ ለቡድናችን ጥሩ አይደለም፡፡ ግን የመጣንበትን አብዛኛውን ነገር ብትመለከተው ነጥብ የጣልንባቸው ያን ያህል በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ብልጫ የተወሰደብን አይደለም፡፡ ከራሳችን አንፃር ስናየው ብዙ ድክመት አለ፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ነጥብ የጣልንባቸውን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች ስትመለከታቸው ጨዋታውን መቆጣጠር ባቃተን ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ የተጫዋች ጥራት የአዕምሮ ጥንካሬ ይጠይቃል ብቁ አድርጎ ማቅረቡ ከአሰልጣኝ ጋር የተያያዘ ነው ከእኛ ውጪ ወደ ሌላ የምትወረውረው አይደለም፡፡”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ኢትዮጵያ ቡናን ለሁለተኛ ጊዜ ከተረከበ ወዲህ በአብዛኛው እንደ ዋና አሰልጣኝ (Head Coach) በእጁ ላይ ያሉትን ተጫዋቾች በማሻሻል እና ሀሳቡን ይበልጥ በማስረፅ ላይ ያተኮሩ ተደጋጋሚ ሀሳቦችን ሲሰጥ የምናውቀው ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሀሳቡን ይበልጥ ሜዳ ላይ ለማውረድ የተሻሉ ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጉት ሲናገር ተደምጧል።

እንደ ቡድን መተግበር ለሚፈልጉት የጨዋታ ሀሳብ ጥራታቸው የላቁ በጫና ውስጥ ኳሱን መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች የማስፈለጋቸው ነገር ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ ባይሆንም አሰልጣኙ በግልፅ ይህን ሲናገር የመደመጡ ጉዳይ ያልተለመደ መሆኑ ትኩረትን ይስባል።

ያጋሩ