የትኩረታችን የመጨረሻ ክፍል የሚሆነው በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን የሚቀርቡበት ነው።
👉 የአዳማ ከተማ የሊጉ ቆይታ ሲጠቃለል
የሊጉ ውድድር ለሁለት ወራት ከተጠጋ ዕረፍት ሲመለስ ውድድሩን የማስተናገዱን ተራ የተረከበችው አዳማ ከተማ ባለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በድምሩ 48 ጨዋታዎችን በጥሩ መንገድ አስተናግዳ በቀጣይነት የማስተናገዱን ኃላፊነት ለተሰጣት ለባህር ዳር ከተማ አስረክባለች።
በርካታ አስገራሚ ሁነቶችን ያስመለከተን የአዳማ የሊጉ ቆይታ የአርባምንጭ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ያደረጉት እና አራት ለአራት የተጠናቀቀውን ጨዋታ ጨምሮ የሮቤል ተክለሚካኤል አስደናቂ ግብ አና ሌሎች በርካታ ሁነቶችን ያሳየን ውድድር ነበር። በድምሩ በአዳማው የሊጉ ቆይታ ከተደረጉ 48 ጨዋታዎች ስድስቱ ብቻ ያለ ግብ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን በድምሩ 110 የሊግ ግቦች ተቆጥረዋል።
በሦስት ነጥብ ልዩነት ሊጉን እየመራ አዳማ የደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ባህር ዳር ሲያመራ በአስር ነጥብ ልዩነት ከተከታዩ ልቆ የሚያመራ ሲሆን በአንፃሩ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው ወደ አዳማ ያቀኑት ጅማ አባ ጅፋር ፣ ሰበታ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ ይገኛል።
በመሰረታዊው የሜዳ ዝግጅት ሆነ ከሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች ውጤታማ የነበረው የሊጉ የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ቆይታ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፍፃሜውን ያገኘ ሲሆን ውድድሩ ከቀጣይ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ የቀሩት የጨዋታ ሳምንታት በባህር ዳር ከተማ የሚስተናገድ ይሆናል።
👉 የጭንቅላት ጉዳት እና የህክምና ዝግጁነት
በጨዋታ ሳምንቱ ወልቂጤ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 3-0 በረታበት ጨዋታ በ20 ደቂቃዎች ውስጥ ያጋጠሙት ሦስት የጭንቅላት ጉዳቶች ጥላ ያጠሉበት ነበር።
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ አጋማሽ በ20 ደቂቃዎች ውስጥ የአርባምንጭ ከተማዎቹ ፀጋዬ አበራ ፣ ፍቃዱ መኮንን እና በወልቂጤ በኩል ደግሞ ዮናስ በርታ ተመሳሳይ የጭንቅላት ጉዳት አስተናግደዋል። ፀጋዬ አበራ ዓይኑ አካባቢ ጉዳት ሲያስተናግድ ፍቃዱ እና ዮናስ ደግሞ ግንባራቸው ላይ ጉዳት ገጥሟቸዋል።
ፀጋዬ አበራ በመጀመሪያ ዙር ህክምና ተደርጎለት በፍጥነት ወደ ሜዳ መመለስ ቢችልም ዳግም መድማት ስላጋጠመው ለሁለተኛው ዙር ህክምና ከሜዳ ለመውጣት ሲገደድ ዘለግ ያለ ደቂቃ ህክምና ተከታትለው ወደ ሜዳ ከገቡት ውስጥ ደግሞ ዮናስ በርታ መድማቱ ሊቆምለት ስላልቻለ በ34ኛው ደቂቃ በፋሲል አበባየሁ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ፍቃዱ መኮንንም እንዲሁ በዕረፍት ሰዓት መልበሻ ክፍል እንዲቀር ተደርጓል።
ይህ አጋጣሚ አሁንም ቢሆን ውስንነቶች ላሉበት የሀገራችን የስፖርት ህክምና እንዲሁም ስለ ጭንቅላት ጉዳት እና መዘዙ ያለውን ደካማ አረዳድ በአደባባይ ያሰጣ አጋጣሚ ነው።
በእግር ኳስ ሜዳ ላይ የሚከሰቱ የጭንቅላት ጉዳቶች ራስን ከመሳት እና ከመድማት በዘለለ በተጫዋቹ መፃኢ የአዕምሮ ጤንነት ላይ አስከፊ መዘዝ የሚያሰከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም መሰል ከጭንቅላት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲከሰቱ በጥንቃቄ መያዝ ያለባቸው ሲሆን በጥድፊያ ለቡድን ጥቅም ሲባል የተጫዋቹን ጤንነት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ በፍጥነት ሚደረጉ ህክምና ሰጥቶ ወደ ሜዳ ማስገባት ከሚኖራቸው መዘዝ አንፃር አሁንም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
👉 የመከላከያ ማርሽ ባንድ
የሊጉ ውድድር ወደ አዳማ ከተማ ካመራ ወዲህ ለወትሮው በአነስተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊዎች ታጅቦ ጨዋታዎችን ያደርግ የነበረው የመከላከያ ስፖርት ክለብ በተሻለ የተነቃቃ የደጋፊዎች ድባብን እያስመለከትን ይገኛል። በአዳማው ውድድር መከላከያ ጨዋታዎችን በሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች የተደገፉ የማርሽ ቡድን አባላት ቡድኑን ሲያበረታቱ እየተመለከትን እንገኛለን።
ከዋናው የእግር ኳስ ቡድን ባለፈ በርከት ባሉ ስፖርቶች የሚካፈለው መከላከያ በጨዋታ ዕለት ሌሎች የቡድኑ ስፖርተኞች በሜዳ ተገኝተው ቡድናቸው የሚያበረታቱ ሲሆን ከእነሱ በተጨማሪ ደግሞ በተለያዩ ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎችን በሚያቀርበው የማርሽ ባንድ ታጅበው የተለየ የድጋፍ ስሜትን እየፈጠሩ ይገኛል።
👉 የደጋፊዎች ተቃውሞ
በጨዋታ ሳምንቱ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል ባህር ዳር በጅማ አባጅፋር እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በመከላከያ ከተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከውጤት አንፃር ጥሩ ያልሆነ ጉዞ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሜዳውን ለቀው ሲወጡ ስታዲየም በታደሙት የክለቡ ደጋፊዎች እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን በአንፃሩ ከሰሞኑ ከውጤት አንፃር መሻሻል አሳይቶ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በመከላከያ በሰፊ የግብ ልዩነት ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ የቡድኑ ደጋፊዎች አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በተለይ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ እንዲሁም ሌሎች የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ላይ በጨዋታ ወቅት እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያሰሙ ተመልክተናል።
👉 በ35 ደቂቃዎች አምስት ጎሎች
በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለክናቸው ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ከተማ እና በሀዲያ ሆሳዕና መካከል እንደተደረገው ጨዋታ በግብ የተንበሸበሸ ጨዋታ አልነበረም። ገና ከጅምሩ በግቦች ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ በድምሩ ስድስት ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች ደግሞ አምስት ግቦች ታይተውበት አልፏል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ብዙ ግብ በተቆጠረባቸው ጨዋታዎች (አርባምንጭ 4-4 ሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ፣ አዲስ አበባ 3-3 ሀዲያ ሆሳዕና) ሁለቱም ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና የነበረባቸው መሆናቸው ቡድኑ ለማስገረም ሆነ ጨዋታዎችን ለመከተል ችግር እንደሌለበት ያሳዩ አጋጣሚዎች ነበሩ።