የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን በሚከተለው መልኩ አዘጋጅተናል።
የተጫዋች አደራደር ቅርፅ – 4-3-3
ግብ ጠባቂ
አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር
ቁመታሙ የግብ ዘብ በ21ኛ ሳምንት እጅግ ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ቡድኑን ግብ ከማስተናገድ ታድጓል። ወደ ሰባት የሚጠጉ ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶች ተሞክረውበት የነበረው አላዛር በጥሩ ቅልጥፍና ፣ የትኩረት ልዕልና እና የውሳኔ አሰጣጥ ሲመክታቸው የነበረበት መንገድ አስገራሚ ነበር። በዋናነት በሁለተኛው አጋማሽ በቅፅበቶች ሦስት ተከታታይ ሙከራዎችን (Triple save) ማዳኑ ያለ ከልካይ በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል።
ተከላካዮች
ወንድማገኝ ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር
ጅማ የውድድር ዓመቱን ድንቅ ጨዋታ ባሳለፈበት ፍልሚያ አስገራሚ ብቃት ያሳየው ተጫዋች ወንድማገኝ ማርቆስ ነው። የመስመር ተከላካዩ ዋነኛ ኃላፊነቱ ከሆነው የመከላከል አጨዋወት በተጨማሪ ወደ ፊት መስመሩን ታኮ በመሄድ ለቡድኑ የግብ ማግኛ አማራጭ ሲሆን ታይቷል። ተቀዳሚ ኃላፊነቱን በመወጣት ደግሞ ከግራ መስመር እየተነሳ ሲያጠቃ የነበረው ዓሊ ሱሌይማንን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ቡድኑን ጠቅሟል።
መሳይ ፓውሎስ – ድሬዳዋ ከተማ
ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ድሬዳዋ ከተማ ከባዱን የወራጅ ቀጠና ፍልሚያ አከናውኖ ሲረታ በታችኛው የፍፁም ቅጣት ምት አልቀመስ ብሎ የነበረው ተጫዋች መሳይ ነው። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ግብ በመሄዱ ረገድ ተሽለው የነበሩት ሰበታዎች ካደረጓቸው አጠቃላይ 13 ሙከራዎች 3ቱን ብቻ ዒላማቸውን እንዲጠብቁ ከአጣማሪው አውዱ ናፊዩ ጋር እጅግ ሲተጋ ነበር።
ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ
በሲዳማው ጨዋታ በቅድሚያ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ከዛም ወደ መሐል ተከላካይነት ተቀይሮ የተጫወተው ሚሊዮን የተጋጣሚ አጥቂዎች በምቾት እንዳይጫወቱ በማድረጉ ረገድ የተዋጣለት ጊዜ አሳልፏል። አልፎ አልፎ ጉልበት እየቀላቀለ ግቡን ላለማስደፈር የሚጥረው ተጫዋቹ በተለይ ከይገዙ ቦጋለ ጋር የነበረው የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎች ተከላካዩ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳዩ ነበሩ።
ብርሃኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
በየሳምንቱ ወጥ ብቃት በማሳየት ቡድኑን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በኩል የሚረዳው ብርሃኑ ባሳለፍነውም ሳምንት በቦታው ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች ቀዳሚ አድርገነዋል። በሦስት አጋጣሚዎች እየተመራ ለነበረው ቡድንየግብ ምንጭ ለመሆን በላይኛው ሜዳ በተደጋጋሚ ሲገኝ አስተውለናል። እርግጥ የሀዲያ የተከላላይ መስመር በጨዋታው ቅርፁን በመጠበቅ ረገድ ደካማ ቢሆንም ብርሃኑ ቡድኑ ግብረ-መልስ እንዲያገኝ የጣረበትን ሂደት ታሳቢ በማድረግ በቦታው መርጠነዋል።
አማካዮች
መስዑድ መሐመድ – ጅማ አባ ጅፋር
ዘንድሮ 1823 ደቂቃዎችን ለጅማ አባ ጅፋር ግልጋሎት የሰጠው አማካይ ባሳለፍነውም ሳምንት በወጥነት እየተጫወተ እንደሆነ ያስመሰከረበትን ጨዋታ አሳልፏል። በተለይ በጨዋታው ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉ ሁለት ኳሶችን ከቆመ አጋጣሚ በጥሩ ልኬት እና እይታ ያቀበለበት መንገድ ተጫዋቹን የሚያስወድስ ነው። ከአሲስቶቹ ውጪም ተቀይሮ እስከወጣበት 80ኛው ደቂቃ ድረስ ከሳጥን ሳጥን በመሮጥ፣ የመልሶ ማጥቃቶችን በማስጀመር እና ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመላክ ቡድኑን አገልግሏል። በመከላከሉም ልምዱን ተጠቅሞ ክፍት ቦታዎችን በመድፈን ያሳየው መታተር አስደናቂ ነበር።
ምንተስኖት አዳነ – መከላከያ
መከላከያ ድንቅ የጨዋታ ቀን አሳልፎ ኢትዮጵያ ቡናን አራት ለምንም ሲረታ በመሐል ሜዳው መልካም ስራን በመስራት ማገር የነበረው ተጫዋች ምንተስኖት ነው። ከወትሮ ለየት ባለ አቀራረብ ወደ ሜዳ በገባው ቡድን ውስጥ ወደ ፊት ተጠግቶ የቡናን የኳስ መቀባበያ አማራጮች ዘግቶ ኳሶችን ለማሸነፍ ሲጥር እንዲሁም አደገኛ የመጨረሻ ኳሶችን በማመቻቸት አይነተኛ ሚና ተወጥቷል። ምንተስኖት ሁለተኛውን የቢኒያም ጎል በጥሩ ሁኔታ ከማመቻቸቱ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን ወደ ሳጥኑ በማድረግ ከአንድም ሦስት ጊዜ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥሮ ነበር።
በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ
የቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው በዛብህ ከአማካይ እየተነሳ የቡድኑ አዳኝ መሆኑን ከተያያዘው ሰንበትበት ብሏል። በ21ኛ ሳምንት ተጫዋቹ ግብ አያስቆጥር እንጂ ኦኪኪ ያስቆጠረውን ጎል ያቀበለው እርሱ ነው። በመታተር ከሳጥን ሳጥን በመሮጥ ሲጫወት የሚታየው በዛብህ በቁጥር በርከት ብለው ሲከላከሉ የነበሩትን የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ለማስከፈት ከእግሩ የሚነሱት ኳሶች አስፈላጊ ነበሩ። በመስመሮች መካከል እየገባም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር ነበር።
አጥቂዎች
አቤል ነጋሽ – አዲስ አበባ ከተማ
በውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት የመዲናውን ክለብ ተቀላቅሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የቋሚነት ዕድል ያገኘው አቤል በአዲሱ ማሊያው ከግብ ጋር የተገናኘበትን ቀን በሀዲያው ጨዋታ አሳልፏል። ከኳስ ጋር ምቾት ያለው አጥቂ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ሲገባ የታየ ሲሆን የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን በማሸነፍም የተሻለ ሥራ ሲሰራ አስተውለናል። ተጫዋቹ በግራ እግሩ እና በቀኝ እግሩ ኳስ እና መረብን ካገናኘ በኋላ የተሟላ ሐት-ሪክ የሚሰራበትን ዕድል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጎሉ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮበታል።
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ አለመኖሩን ተከትሎ የመሐል አጥቂ ከሆነ የሰነባበተው አማኑኤል በቦታው ከጨዋታ ጨዋታ እያደረገ ያለው ብቃት እየጨመረ ነው። እርግጥ ተጫዋቹ ከጎል ጋር በቀጥታ በተደጋጋሚ ባይገናኝም ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት፣ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ቦታዎችን በማሸነፍ እንዲሁም በእንቅስቃሴው የተከላካዮችን ትኩረት በመበታተን አጋሮቹ ክፍተት እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል ትልቅ አበርክቶ ያደርጋል። በሀዋሳውም ጨዋታ ከኳስ ውጪ ሀሰተኛ ሩጫዎችን በማድረድ፣ የመልሶ ማጥቃቶችን በማስጀመር እና በወሳኝ ቦታዎች ላይ በመገኘት ያሳየው ብቃት የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ እንዲሆን አስችሎታል።
ተሾመ በላቸው – መከላከያ
ከጦሩ በምርጥ ቡድናችን የተካተተው ሌላኛው ተጫዋች ተሾመ ነው። ከቀኝ መስመር እየተነሳ ወደ ሳጥን እንዲገባ ኃላፊነት የተሰጠው ተሾመ በጨዋታው አስደናቂ ብቃት በማሳየት የመክፈቻውን ጎል ራሱ በማስቆጠር ሦስተኛውን ጎል ደግሞ አሲስት በማድረግ በስሙ አስመዝግቧል። ወጣቱ አጥቂ ፍጥነቱን በመጠቀም በተደጋጋሚ በተከላካዮች ጀርባ እና መሐል እየተገኘ የፈጠራቸው ሌሎች የግብ ማግባት አጋጣሚዎችም ለቡናዎች እጅግ ፈተናን የሰጡ ነበር። ከኳስ ውጪም የመታተር ባህሪ የታየበትን ተጫዋች በምርጥ ቡድናችን ውስጥ የመስመር አጥቂ አድርገን ሰይመነዋል።
አሠልጣኝ
ዮርዳኖስ አባይ – መከላከያ
በ21ኛ ሳምንት የሱፍ ዓሊ እና ኃይሉ ነጋሽ ለምርጥነት የሚያበቃ ተግባር በየቡድኖቻቸው ቢሰሩም አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በሌሉበት በድኑን እየመራ ወደ ሜዳ የገባው የመከላከያው ምክትል አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ተመራጫችን ሆኗል። ለወትሮው ግብ ማስቆጠር ከብዶት የሚታየው እና ለተጋጣሚዎቹ ከፍ ያለ ግምት በመስጠት ወደ ሜዳ በመግባት የሚታማው መከላከያ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ፍፁም የተለየ ባህሪን አሳይቷል። ባለፉት ጨዋታዎች የማጥቃት ተነሳሽነቱን ለማሻሻል ጥረት ላይ እንደሆነ ምልክት ቢሰጥም አሰልጣኙ ቡድኑን በመራበት በቡናው ጨዋታ ግን የተጋጣሚውን አቀራረብ በማክሸፉ ረገድ የተዋጣለት ዕቅድን በመተግበር እና ተደጋጋሚ ዕድሎችን ፈጥሮ አራት ግቦችን በማስቆጠር ጣፈጭ ድልን አጣጥሟል።
ተጠባባቂዎች
ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ
ዋሀብ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ
ዓለምብርሃን ይግዛው – ፋሲል ከነማ
ቢኒያም በላይ – መከላከያ
አዲሱ አቱላ – መከላከያ
በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ
ሪችሞንድ አዶንጎ – አዲስ አበባ ከተማ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ