የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል ሁለት ክለቦች ላይ የገንዘብ ቅጣት ሲጥል በአንድ ክለብ ላይ ደግሞ የገንዘብ እና ያለደጋፊ የመጫወት ውሳኔ አሳልፏል።

በአዳማ ከተማ ለስድስት ሳምንታት ሲደረግ የነበረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ቀናት በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በ21ኛው ሳምንት የሊጉ የመጨረሻ የአዳማ ጨዋታዎች ላይ ክለቦች በፈፀሙት የዲሲፕሊን ግድፈት የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ሥነ ስርአት ኮሚቴ ሦስት ክለቦች ላይ የቅጣት በትር አሳርፏል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ቡና በመከላከያ 4-0 በሆነ ውጤት ሲሸነፍ የክለቡ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እና የክለቡ አመራሮች ላይ በሰነዘሩት አፀያፊ ስድብ የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ ስርአት ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ክለቡ የፈፀመውን ድርጊት ዳግም በመፈፀሙ በክለቡ ላይ የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ የ22ኛ እና የ23ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከወልቂጤ እና ከድሬዳዋ ጋር ሲያደርግ ያለደገፊዎቹ እንዲጫወት ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡

በሌላ የቅጣት ዜና አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን በፈፀመበት ወቅት የክለቡ ደጋፊዎች በውድድር አመራሮች ላይ አፀያፊ ስድብ በመሰንዘራቸው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች ከዚህ ቀደም የተጣለባቸውን ድርጊት ታሳቢ በማድረግ የ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰበታ ከተማ በድሬዳዋ ሽንፈት ባስተናገደበት ዕለት የሰበታ ደጋፊዎች የውድድር አመራሮችን መሳደባቸው በሪፖርት በመቅረቡ በክለቡ ላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፏል፡፡ በተያያዘ ዜና በተጫዋቾች ረገድ በተጣለ ቅጣት የሀዋሳ ከተማው የመስመር ተከላካይ መድሀኔ ብርሀኔ ተከታታይ አስር ቢጫ ካርድ ማየቱን ተከትሎ የሁለት ጨዋታዎች ዕገዳ እና የሁለቴ ጨዋታ ቅጣት ተቀጥቷል፡፡

ያጋሩ