አዲስ አበባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በቀርቡ ከአሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጋር በስምምነት የተለያየው አዲስ አበባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል።

ከ2009 በኋላ ዘንድሮ ወደ ሊጉ የተመለሰው አዲስ አበባ ከተማ በምክትልነት ዓመቱን ጀምረው ወደ ዋና አሰልጣኝነት ሚና ከመጡት አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጋር ቆይቶ በቀናት በፊት በስምምነት መለያየቱ ይታወሳል። በዚህ መሠረት አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር የተለያዩ እንስቃሴዎች ያደረገው ክለቡ በስተመጨረሻም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ መቅጠሩን አረጋግጠናል። አሰልጣኝ ጳውሎስም ከወልቂጤ ጋር ያላቸውን ጉዳይ አጠናቀው ፊርማቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አኑረዋል።

በተጨማሪም የአሰልጣኝ ደምሰው ምክትል የነበሩት አሰልጣኝ አሳምነው በተመሳሳይ በስምምነት መለየየታቸውን ተከትሎ የአሰልጣኝ ጳውሎስ ረዳት በመሆን አብረዋቸው እንዲሰሩ አሰልጣኝ እዩብ ማለን መሾማቸውን አውቀናል። ዛሬ ረፋድ ላይ ቡድኑን ተረክበው የማሰልጠን ሥራቸውን ለመጀመር ወደ ባህር ዳር የሚያቀኑ ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታቸውንም በ22ኛ ሳምንት ከቀድሞ ክለባቸው ወልቂጤ ከተማ ጋር የሚያደርጉ ይሆናል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ፣ ባህር ዳር ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ያሰለጠኑባቸው ክለቦች ናቸው።

ያጋሩ