በነገው ዕለት በባህር ዳር በሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ የዳኝነት ሚና መተግበር እንደሚጀምር ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የአራተኛ ከተማ ውድድሩን ከነገ ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ማከናወን ይጀምራል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ሦስት ከተሞች ውድድር ላይ መጠነኛ የዳኝነት እፀፆች ሲስተዋሉ የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ ጎል ጋር ከመስመር ያለፉ እና ያላለፉ ኳሶች ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም። የተሻለ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሌለውን የሀገራችን ዳኝነት ውሳኔዎች ለማሳደግ ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የዳኝነት ሚና መተግበር እንደሚጀምር ይፋ ሆኗል።
በአሁኑ ሰዓት በባህር ዳር አዝዋ ሆቴል የውድድሩ የበላይ አካል ከክለብ ተወካዮች ጋር እያደረገ በሚገኘው ስብሰባ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ተወካይ እና የጨዋታ ኮሚሽነር የሆኑት አቶ አዲሱ ነጋሽ ከነገ ጀምሮ ስድስት ዳኞች በጨዋታዎች እንደሚመደቡ ተናግረዋል። ከዋና እና ሁለት የመስመር እንዲሁም አንድ አራተኛ ዳኛ ውጪ የሚጨመሩት ሁለት የጎል አጠገብ ዳኞች እንደሆኑ ተገልጿል።