ከሀዋሳ ከተማ በውሰት ውል ከተገኘው እና ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ ከሚገኘው የጅማ አባ ጅፋሩ ወጣት ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ባህር ዳር ከተማን 2-0 የረታበትን ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተ ሰው ጅማ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ያለ ቡድን ነው ብሎ ለመገመት ይቸገራል። ከቡድኑ ባለፈ ደግሞ በሁለቱ ብረቶች መሀል የቆመው ግብ ጠባቂ ዘለግ ያለ ልምድ ባለቤት እና በብሔራዊ ደረጃ ተመራጭ የሆነ ተጫዋች እንደሆነ ቢያስብ አያስገርምም። ተጫዋቹ ሰባት ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን ከማዳኑ በተጨማሪ 58ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ጊዜ የተደረጉበትን ሦስት ተከታታይ ኳሶች ያመከነበት መንገድ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። ይህን ጀብድ የፈፀመው ግብ ጠባቂ ግን ከሚያሳየው እንቅስቃሴ በተቃረነ ሁኔታ በሊጉ በወጥነት የመጫወትን ዕድል ያገኛው ገና ዘንድሮ ነው ፤ የሀዋሳ ከተማ ፍሬ የሆነው አላዛር ማርቆስ።
በአያቶቹ እጅ ያደገው እና ትውልዱ በሀዋሳ ከተማ ቀበሌ 06 የሆነው አላዛር በቄራ ሜዳ ነበር በለጋነት ዕድሜው ከእግርኳስ ጋር የተዋወቀው። ከጅምሩ ግብ ጠባቂነትን ምርጫው ያደረገው ታደጊው እንደ ዓርዓያነት የሚያውን የእግርኳስ ሰው ለማግኘት ዕሩቅ ማለም አልተጠበቀበትም ፤ ምክንያቱም ሦስት አጎቶቹ በጊዜው ለእግርኳስ ቅርብ ነበሩ። ጌታሁን ባፋ (አሁንም በነቀምት ከተማ የሚጫወት) ፣ በቀለ ባፋ (ቀደም ሲል በተጨዋችነት አሁን ደግሞ በዳኝነት ሙያ ውስጥ የሚገኝ) እና ይስሀቅ ባፋ (እግርኳስን በጉዳት ምክንያት በቶሎ ያቆመ) አላዛር የአያቶቹን ‘እግርኳስ ይቅርብህ’ ሀሳብ ተቋቁሞ በስፖርቱ እንዲዘልቅ የትጥቅ እና የሀሳብ ድጋፍ እያደረጉለት በጊዜ ከእግርኳስ ጋር እንዲወዳጅ አድርገውታል።
አላዛር ዕድሜው ከፍ ሲል በቅድሚያ በሰፈር ውስጥ በአብርሃም ፕሮጀክት በመቀጠል ደግሞ ሙሉጌታ ምህረት እና ዘሪሁን ቀቀቦ አማካይነት በተቋቋመው ዛማ ፕሮጀክት ውስጥ የማለፍ ዕድልን አግኝቷል። በመቀጠል ከፕሮጀክት ህይወቱ ከፍ ብሎ የሀዋሳ ከተማን ‘C’ ቡድን መቀላቀል ሲችል በ’B’ ቡድኑ እና በተስፋ ቡድኑ ውስጥ አልፎ 2013 ላይ በፕሮጀክት ደረጃ በሚያውቀው ሙሉጌታ ምህረት አማካይነት የዋናው የኃይቆቹ ቡድን አባል መሆን ቻለ።
በሀዋሳ ከተማ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች ውስጥ በነበሩት ዓመታት ግን አንድ “የግብ ጠባቂነት ህይወቴን ሀ ብዬ የጀመርኩት በእሱ ነው ማለት እችላለሁ” ብሎ የሚገልፀው አጋጣሚን በ ‘B’ ቡድን ውስጥ እያለ ማግኘት ቻለ። ይኸውም 2010 ላይ በታንዛኒያ በተደረገው የ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የመካተት ዕድል ነበር። አሰልጠኝ ተመስገን ዳና በዕድሜ ምክንያት ተቀናሽ በነበሩ ተጫዋቾች ቦታ ይህንን ታዳጊ ግብ ጠባቂ ይዞ ወደ ውድድሩ አመራ። አላዛር ይህንን አጋጣሚ በልዩነት የሚያስታውሰው እና በተጫዋችነት ህይወቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድም በለጋ ዕድሜው በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተመራጭ በመሆኑ ሁለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን በቻለ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ስር የመሰልጠን በር ስለከፈተለትም ነው። በውድድሩ በቀድሞው ግብጠባቂ እና የአሁኑ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በለጠ ወዳጆ አማካይነት ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቶ ገና በመጀመሪያው ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ዓይን ውስጥ መግባት ሲችል እስከ ፍፃሜው በዘለቀው የU17 ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ባሳየው እንቅስቃሴ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ መመረጥም ቻለ።
ከሴካፋው ውድድር መልስ የአላዛር ዕድገት ይበልጥ ፍጥነቱን ጨመረ። በሀዋሳ ከተማ ከ’B’ ወደ ተስፋ ቡድን አድጎ 2011 እና በኮቪድ ምክንያት ባልተጠናቀቀው የ2012 የውድድር ዓመት በዚሁ ቡድን ውስጥ ካሳለፈ በኋላ አምና ስሙ በፕሪምየር ሊጉ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ተካተተ። ሆኖም ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ዳግም ተፈራ እና ምንተስኖት ጊንቦ በነበሩበት ቡድን ውስጥ አላዛር እንደሚገመተው ሁሉ በመጀመሪያ ዓመቱ እምብዛም የመሰለፍ ዕድልን አላገኘም። ዘንድሮም ሜንሳህ ክለቡን ቢለቅም ጋናዊው መሀመድ ሙንታሪ ወደ ኃይቆቹ ቤት ማምራቱን ተከትሎ ምንም እንኳን ጥሩ ተስፋን ቢያሳይም ተጫዋቹ በርካታ የጨዋታ ደቂቃዎችን የማግኘት ዕድሉ ጠባብ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነበር። በዚህ መሀል ግን አንድ አዲስ ነገር ተፈጠረ።
ጅማ አባ ጅፋርን የተረከቡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስባቸውን ለማጠናከር አማራጮችን ሲፈልጉ የሀዋሳው ታዳጊ ግብ ጠባቂ በልምምድ ላይ የሚያሳየው ብቃት ወደ ቡድናቸው እንዲያመጡት መነሻ ሆናቸው። ሆኖም በአሰልጣኞቹ በኩል የመጣውን የአንድ ዓመት የውሰጥ ጥያቄ አላዛር አልተቀበለውም። ጥሩ ተስፋ እያሳየ የነበረበት የትውልድ ከተማውን ክለብ ሀዋሳ ከተማን በድንገት የመለየቱ ሀሳብ ሊያውም በሀገራችን ባልተለመደው የውሰት ውል ለዓላዛር ብዙም የሚዋጥ አልሆነም። ነገር ግን የጅማ ጥያቄ በዚህ ሳይቆም ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ ተደጋገመ። ይህን ጊዜ ግን ተጫዋቹ ጉዳዩን ከአሰልጣኞቹ እና ከቤተሰቦቹ ጋር መከረበት። የመጨረሻው ውሳኔውም ከሀዋሳ በተሻለ ቀለል ያለ የመሰለፍ ፉክክር ሊኖረው በሚችለው የጅማ ቡድን ውስጥ መካተት ከፍ ያለ ደቂቃ እንደሚያስገኝለት አመነ። እናም ወጣቱ ግብ ጠባቂ ወደ ምዕራቡ ቡድን ለማምራት ተስማማ።
የጅማ አጀማመሩ ግን አስደሳች አልሆነም። ቡድኑ በአራተኛው ሳምንት ጨዋታውን ሲያደርግ ዓላዛር በቀዳሚ ተሰላፊነት በጀመረበት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ የ3-1 ሽንፈት ሲያስተናግድ አላዛርም ጥሩ የጨዋታ ቀን ሳያሳልፍ ቀረ። አላዛር ይህንን ጨዋታ በልዩነት ያስታውሰዋል። “ሁለት ልምምድ ከሰራሁ በኋላ ነው የገባሁት። የተጨዋቾቹን ስም እንኳን በደንብ አላውቅም ነበር። እንደመጀመሪያ እንቅስቃሴዬም ብዙም አልነበረም። ጨዋታውን 3-1 ተሸነፍን ፤ እኔም ወደ ቤንች ወረድኩ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አለፈኝ። ሦስተኛው ጨዋታ ላይ በድጋሜ ዕድል አገኘሁ። በሂዱት ከተጨዋቾች ጋርም እየተላመድኩ ቀስ በቀስ አሁን ወዳለሁበት ሁኔታ ደረስኩ። የመጀመሪያ ጨዋታ ሲሆን ምንም ደፋር ብትሆን ሊበላሽብህ ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ተበላሽቶብህ ስህተትህን አውቀህ እያስተካከልክ ብትሄድ ይሻላል በኋላ ላይ ከሚበላሽብህ። በመሆኑም ያ ጨዋታ አሁን ላለሁበት ነገር ትልቅ ስንቅ ነው የሆነኝ። ከዛ በኋላ ራሴን በደንብ ፈትሼ ልምምዴን በአግባቡ በመስራት ያለኝን ነገር በማሳደግ ላይ እገኛለሁ።” ይላል።
እንዳለውም ያ ጨዋታ በሽንፈት ይደምደም እንጂ አላዛር ዳግም ወደ ተሰላፊነት ከተመለሰበት እና ጅማም ሌላ ሽንፈት ካስተናገደበት የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በኋላ በሂደት የጅማ አባ ጅፋር ቀዳሚ ተመራጭ መሆን ችሏል። ከዚያ በኋላም በ15 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በመጫወት የዘንድሮው የሜዳ ላይ ደቂቃዎቹን 1350 ማድረስ ችሏል። በእርግጥ አላዛር ከ15ቱ ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣው በአምስቱ ብቻ ነው። ነገር ግን ጅማ አባ ጅፋር እጅግ ደካማ አቋም ባሳየባቸው ጨዋታዎች በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፎ እንዳይወጣ የሚያደርገው የአላዝር ብቃት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በየጨዋታው እጅግ ለግብ የቀረቡ ኳሶችን በአስደናቂ ቅልጥፍና ሲያመክን መታየቱ የብዙዎቹ ዓይን ማረፊያ አድርጎታል።
የቡድኑ ደካማ የተከላካይ መስመር እና አጠቃላይ ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት የመከላከል አደረጃጀት በርካታ የግብ ሙከራዎችን እንዲያስተናገድ ማድረጉ እና ግብ ጠባቂውም አብዛኞቸን ማዳኑ ነጥሮ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል። “ለምሳሌ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ብቃት የሚታወቅ ነው። ግብ ጠባቂው አይወድቅም ፤ የአየር ላይ ኳስ ቢመጣ ከስንት አንዴ ነው። ጠንካራ ተከላካይ ሲኖርህ በሥነልቦናም ጠንካራ ትሆናለህ። ምክንያቱም ኳስ እነሱን በቀላሉ አልፎ አይመጣም። እኛ ጋር ደግሞ በብዛት እንደኔ ሁሉ ወጣት የሆኑ ተከላካዮች ናቸው በብዛት ያሉት። እና ከእነሱ የሚመጣውን ኳስ እኔ ነኝ የምቀበለው ያ የመታየት ዕድል ሰጥቶኛል። የዛን ያህል ደግሞ ያጋፍጣልም።” የሚለው አላዛር የቡድኑ ለተጋጣሚ በርካታ የግብ ዕድል የመፍቀድ ድክመት ፈተናም መልካም አጋጣሚም እንደሆነለት ይጠቁማል።
አላዛርን ከዕድሜው ከፍ ያለ ግብ ጠባቂ ከሚያስብሉት ጠንካራ ጎኖቹ ውስጥ አንዱ ምናልባትም ዋነኛው ከፍ ያለ በራስ መተማመኑ ነው። በተለይም ከግብ ክልሉ ወጣ ብሎ ከአጥቂዎች ጋር አንድ ለአንድ የሚፋለምባቸው ቅፅበቶች ላይ የጊዜ አጠባበቁ እና እርግጠኝነቱ በርካታ ኳሶችን ወደ መረቡ ከሚያደርጉት ጉዞ አግዷል። “በአንዴ የሚመጣ ነገር ሳይሆን በፊትም የነበረ ነው። አምናም የጨዋታ ዕድልም ባላገኝ ልምምድ ላይ እጠቀመው ነበር። እነዛ ነገሮች አሁን ሜዳ ላይ ሲፈጠሩ ያኔ የሰራሁት ጠቅሞኛል።” ሲል ይህ አቅሙ አብሮት የነበረ እንደሆነ የሚገልፀው አላዛር
በዚህ መጠን ጎልብቶ እንዲታይ ስላደረገው የውሰት ውልም አንስተንበታል።
ጅማ ራሱን ለማጠናከር የመረጠው ይህ የውሰት አካሄድ ቡድኑን ከመጥቀሙ ባለፈ በየክለቡ ከተጠባባቂነት የዘለለ ሚና ሳይኖራቸው በየዓመቱ ለምንመለከታቸው ግብ ጠባቂዊች ጥሩ ማሳያ መሆን ይችላል። “ከስንት አንዴ የሚገኝ አጋጣሚ ነው። በየቡድኑ ብዙ አቅም ኖሯቸው የተቀመጡ ግብ ጠባቂዎች አሉ። በተለይ የመጀመሪያው ግብ ጠባቂ የውጪ ዜጋ ከሆነ ዕድል አግኝተው ጥሩ ቢንቀሳቀሱ እንኳን መልሰው ቦታውን መነጠቃቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ በእንቅስቃሴው ጥሩ ብትሆን እንኳን በሥነልቦናው እንድትወርድ ያደርጋል። እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ቢሆን ግብ ጠባቂዎች አሉ። አሰልጣኞች ዓይናቸውን መክፈት አለባቸው።” የሚለው የዓላዛር ሀሳብም ይህ ጅምር ተጠናክሮ ቢቀጥል በቀጣይ ዓመታት በግብ ጠባቂዎች በኩል ያለው እጥረት በአዳዲስ ስሞች ተቀርፎ ልናይ የምንችልበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው።
የግብ ጠባቂዎች ነገር ሲነሳ በሊጉ በየጨዋታው ለማለት በሚያስደፍር የቁጥር ብዛት ከመታየት አልፈው በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሳይቀር ዋጋ ያሚያስከፍሉ ግለሰባዊ ስህተቶችን አለማንሳት ይከብዳል። በውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች በስፋት ተይዞ የነበረው የክለቦች የግብ ጠባቂነት ቦታ በተለይ ዘንድሮ በሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች እየተተካ በብዙዎች ዘንድ ሲበረታታ የሚታየውም ተጫዋቾቹ ከደቂቃ ብዛት ስህተት ይቀንሳሉ በሚል ተስፋ ነው። በትክክልም ብዙ ደቂቃ ማግኘት ግብ ጠባቂን እንደሚያሳድግ የዓላዛር የዘንድሮ የውድድር ዓመት ማሳያ ቢሆንም ለእርሱ ግን በሀገር ውስጥ እና በውጪ ግብ ጠባቂዎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፋ ያለ ሀሳብ ነው።
“እኛ ሀገር ማንኛውም ግብ ጠባቂ በአግባቡ በፕሮጀክት የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አግኝቶ የሚያልፍ የለም። አሁን አሁን ነው የተማሩ እና በሙያው ውስጥ ያለፉ አሰልጣኞች የመጡት እንጂ በፊት ዝም ብለን ነበር የምንሰራው። ወድቆ መመለስ እንጂ ቴክኒክ ምናምን አልነበረም። በዚህ መንገድ መጥተን ነው ቀጥታ ከውጪዎቹ ጋር የምንወዳደረው። እነሱ በሀገራቸው ከፕሮጀክት ጀምሮ በየደረጃው ተሰርቶባቸው ነው እዚህ ደረጃ የሚደርሱት። እንደውም እኛ በግላችን ልፋት እዚህ መድረሳችን ልንደነቅ ይገባል። በፍላጎት ደረጃ ራሱ አሰልጣኝ ሳይኖርህ ግብ ጠባቂ ለመሆን ማሰብ ከባድ ነው። ፕሮጀክት ቢኖር እንኳን አንድ አሰልጣኝ እንጂ ለግብ ጠባቂ ለብቻው አይኖርም። ስለዚህ በራስህ ነው የምትሰራው እንጂ ታዳጊ ሆነህ የቴክኒክ ሥራዎችን ልታውቅ አትችልም። ዝም ብሎ መውደቅ ነው። የውጪዎቹ ግን የቴክኒክ ሥራዎችን ሁሉንም ያውቃሉ እኛ ግን ገና እያደገን ስለሆነ የተማረም ሰው ገና እየመጣ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ያለው ነገር እየተስተካከለ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ።” የሚለው የግብ ዘብ እሱም በሥልጠና ህይወቱ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሲመረጥ እንደነበር ለማሳያነት ያስቀምጣል።
በዚህ መልኩ በራሱ የተጫዋችነት ህይወት ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ የኢትዮጵያ እግርኳስ የግብ ጠባቂዎች ዕድገት ላይ በትልቁ ተስፋ የሚያደርገው አላዛር የዘንድሮው ብቃቱ የሚያጨበጭብ ቢሆንም ከፊት ረጅም ርቀት መጓዝ ይጠበቅበታል። “ገና ሀ ብዬ ነው የጀመርኩት በጣት የሚቆጠር ጨዋታ ነው ያደረኩት። ታዳጊ ነኝ ፤ ብዙ የሚቀረኝ ነገር አለ። ብዙ የሚጠበቅብኝ ነገር አለ።” በሚል ያለበትን ደረጃ የሚገልፀው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ቀሪ የእግርኳስ ዘመኑን በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ በሚኖረው ህይወቱ በትክክለኛው የፕሮፌሽናሊዚም መንገድ ሙያውን አክብሮ በትጋት መስራት እንዳለበት በቅጡ የተረዳ ይመስላል።
ስለቀጣይ ጊዜያት ሲያስብ አሁን ላይ እንደመጀመሪያ የውድድር ዓመት ያሳየውን ብቃት ማስቀጠል እና የቀሩትን ጨዋታዎች ከጅማ ጋር በበጎው መልኩ መጨረስ ቀዳሚ ዓላማው መሆኑን የነገረን ዓላዛር ማርቆስ በእስከዛሬው የእግርኳስ ህይወቱ ዘርዝሮ የማይጨርሳቸው በዙሪያው ለነበሩ ግለሰቦች ስላደረጉለት ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል። በተለይም በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያካተተው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ፣ ለተስፋ ቡድን አሰልጣኙ እና የውሰት ውሉን እንዲቀበል ላማከረው ብርሀኑ ፈየራ ፣ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ላመጡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና ራሱን በወጥነት እንዲያሳይ ላደረገው የቡድኑ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሀመድ ጀማል ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል።