ነገ ፕሪምየር ሊጉ ባህር ዳር ላይ ሲቀጥል በሚደረጉት ሦስት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ አርባምንጭ ከተማ
በ21ኛ ሳምንት የውድድር ዓመቱ አራተኛ ድሉን ባህር ዳር ከተማ ላይ ያገኘው ጅማ አባ ጅፋር በጊዜያዊ አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊ እየተመራ በምርጥ ብቃት ጨዋታውን አገባዷል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሙጥኝ ያለው ቡድኑ ነገ በሚጀምረውን የሊጉ የመጨረሻ ምዕራፍ ውድድር ማሸነፍ ካልቀጠለ በቀጣዩ ዓመት በከፍተኛው የሊግ ዕርከን መክረሙ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። ይህንን ተከትሎም ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ያገኘውን ድል ማስቀጠል ግዴታው ነው። በተጫዋቾች ጥራት እና ጥልቀት የሚበልጠውን የባህር ዳር ሰራዊት እጅ ባሰጠበት ጨዋታ ያሳየውን ከኳስ ጋር እና ውጪ መታተር ደግሞ መድገም ይጠበቅበታል። እርግጥ አርባምንጭ ከኳስ ጀርባ መሆንን የሚያዘወትር ቡድን ስለሆነ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንደሚኖረው ግልፅ ነው። ይህንን የኳስ ቁጥጥር ግን ፍሬያማ ለማድረግ በድርብ የአራት ተጫዋቾች የሚሰራውን ግንብ (Double block of four) ለማስከፈት እጅግ መትጋት አለበት።
ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ካጋጠመው ሽንፈት ባሳለፍነው ሳምንትም ያላገገመው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ 10ኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም የወራጅነት ስጋት ያንዣብብበታል። በ20 የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ከሁለት ጎል በላይ ያስተናገደው ስብስቡ ባሳለፍነው ሳምንት ሳይጠበቅ ሦስት ግቦችን ለወልቂጤዎች እንካችሁ ብሏል። እርግጥ በጨዋታው በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ ባይሆንም በሁለቱ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንካራ አለመሆኑ እንዲረታ ያደረገው ይመስላል። የነገው ተጋጣሚ ጅማ ግን በሊጉ ሁለተኛው ብዙ ግብ የሚገባበት እና ትንሽ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ስለሆነ በአንፃራዊነት ወደ ቀደመ ብቃቱ ለመመለስ ያን ያህል እንደማይቸገር ይታመናል። ከአዳማ ከተማ በመቀጠል ብዙ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው የአሠልጣኝ መሳይ ስብስብ ከላይ እንደገለፅነው ኳሱን በመተው ሽግግሮችን እንዲሁም ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም አደጋ ለመፍጠር እንደሚጥር ይታመናል።
ጅማ አባ ጅፋር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ከሆኑት ተጫዋቾች መካከል መሐመድኑር ናስርን በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት በነገው ጨዋታ የማያገኝ ሲሆን ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት ወደ ልምምድ እንደተመለሰለት ተሰምቷል። የቅጣት ዜና የሌለበት አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ጉዳት ላይ የሚገኙት አህመድ ሁሴን እና አንድነት አዳነን ግልጋሎት አያገኝም።
ይህንን ጨዋታ ሚካኤል ጣዕመ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት አሸብር ታፈሰ እና አብዱ ይጥና በረዳትነት ተስፋዬ ገርሙ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በእስካሁኖቹ ሦስት ግንኙነታቸው ሁለት ጊዜ ያለግብ ሲለያዩ ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በ3-1 ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
አላዛር ማርቆስ
ወንድማገኝ ማርቆስ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ
መስዑድ መሀመድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – አድናን ረሻድ
ኢዮብ ዓለማየሁ – ዳዊት ፍቃዱ – ሱራፌል ዐወል
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ወርቅይታደስ አበበ – ማርቲን ኦኮሮ – በርናንድ ኦቼንግ – ተካልኝ ደጀኔ
ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ፀጋዬ አበራ
ኤሪክ ካፓይቶ – በላይ ገዛኸኝ
ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ላለመውረድ በሚፋለመው መከላከያ የአራት ለምንም አሰቃቂ ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ብቃቱ ጥሩ አይደለም። ውድድሩ ለአምስት ቀንም ቢሆን ተቋርጦ በሌላ ከተማ መደረጉ ደግሞ ካለበት ድባቴ እንዲወጣ እንደሚያደርገው ይገመታል። በመከላከያው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በጅማውም ጨዋታ ከአዎንታዊ ጎኑ አሉታዊ ጎኖቹ አመዝነውበት የታዩት ቡድኑ ወደ ቀደመ ቅኝቱ በቶሎ መግባት የግድ ይለዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ቦታ የተቀመጠው ስብስቡም ከሌላኛው ላለመውረድ እየታገለ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጋር መጫወቱ ወደ ቀደመ ብቃቱ ለመመለስ የሚያደርገውን ሩጫ ፈተና እንዳያበዛበት ያሰጋል። የሆነው ሆኖ ግን ቡና የሚታወቅበትን ከኳስ ጋር የማሳለፍ ጊዜ ነገም ዘለል ላሉ ደቂቃዎች እንደሚከውነው ሲጠበቅ በላይኛው ሜዳ የሚኖረውን የተጫዋች ክምችት አልፎ ግብ ለማስቆጠር ግን በቁጥር በዝቶ ከማጥቃት ጀምሮ ሜዳውን መለጠጥ፣ ሀሰተኛ ሩጫዎችን ማዘውተር እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን በመላክ ጥራት ያላቸው ዕድሎችን መፍጠር ይጠበቃል።
ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ከተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በተቃረነ ተነሳሽነት ላይ ይገኛል። ብርቱካናማዎቹ አሁንም ከወራጅ ቀጣናው ዞን ርቀዋል ማለት ባይቻልም የአዳማ ከተማ የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ግን ለቀጣዩ ጊዜ ስንቅ የሚሆኑ ናቸው። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስቆጥረው ሰባት ነጥቦችን ማሳካታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም ከዚያ ቀደም ቡድኑ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ ነበር ያሳካው። የአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ቡድን በአሰላለፍ እና በአጨዋወት ምርጫው ላይም ለውጦችን አድርጎ ተመልክተነዋል። ለወትሮው ኳስ ይዞ ለመጫወት ይጥር የነበረው ቡድን አሁን ላይ ፈጠን ያሉ ጥቃቶችን መሰንዘር ምርጫው ሆኖ ይታያል። ነገም መሀል ሜዳ ላይ የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ በቁጥር ብልጫ በማፈን እና ኳሶችን በማስጣል ጥሩ አቋም ላይ በሚገኘው ሄኖክ አየለ ለሚመራው የፊት መስመሩ የሚሆኑ ኳሶችን ማድረስ ዋነኛ የማጥቃት አማራጩ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ቡና ሮቤል ተክለሚካኤልን በቅጣት ሚኪያስ መኮንን ደግሞ በጉዳት ምክንያት በዚህ ጨዋታ ላይ አያሰልፍም። አቡበከር ናስር ፣ አቤል እንዳለ እና ስዩም ተስፋዬ ግን መመለሳቸው ተሰምቷል። በድሬዳዋ በኩል ደግሞ ያሲን ጀማል በቅጣት ዳንኤል ኃይሉ በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ጉዳት ላይ የነበረው እንየው ካሳሁን እና በቅጣት አንድ ጨዋታ ያለፈው ዳንኤል ደምሴ ወደ ስብስቡ ተመልሰዋል።
ለዚህ ጨዋታ መሀል ዳኛ በመሆን ባህሩ ተካ በረዳትነት ካሳሁን ፍፁም እና ተከተል በቀለ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ዮናስ ማርቆስ ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡስኖች እስካሁን 19 ጊዜ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 11 ድሬዳዋ ከተማ 3 ድሎችን አስመዝግበው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና 32 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – ስዩም ተስፋዬ
ዊሊያም ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሠ ሰለሞን
ተመስገን ገብረኪዳን – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ
ድሬዳዋ ከተማ (3-5-2)
ፍሬው ጌታሁን
አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – ከድር ኸይረዲን
እንየው ካሳሁን – ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ – አቤል አሰበ – ጋዲሳ መብራቴ
ሙኸዲን ሙሳ – ሄኖክ አየለ
ሀዲያ ሆሳዕና ከ መከላከያ
ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላገኛቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወደ ላይኛው ፉክክር ለመጠጋት በጥረት ላይ ይገኛሉ። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ስድስት ግቦችን ማስቆጠራቸው በተለይም በማጥቃቱ ረገድ አሁን ላይ ስላሉቡት ደረጃ የሚናገር ቁጥር ነው። ግብ በማስቆጠር ድክመቱ ይታወቅ የነበረው መከላከያም ኢትዮጵያ ቡና ላይ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ነው ወደዚህ ጨዋታ የሚመጣው። ከግቡ ቁጥር መብዛት በተጨማሪ ጦሩ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የመመለሱ ነገር ለነገው ፍልሚያ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆነው ይገመታል። በውድድሩ የአዳማ የመጨረሻ ቆይታ ቡድኖቹ ላይ ከታየው መነቃቃት አንፃርም ይህ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ይገመታል።
እስከመጨረሻው ደቂቃ የመፋለም ባህሪን እያስመለከቱን የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ለማጥቃት የሚሰጡት ቦታ ከፍ ማለት ግቦችን ቢያስገኝላቸውም ከኋላ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው ይገኛል። ይህ ድክመታቸው መከላከያ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ከተገበረው ከፍ ያለ ጫና እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር አንፃር ሲታይ ዳግም ፈተና ሊደቅንባቸው ይችላል። የማጥቃት አጨዋወቱን በሂደት እያሳደገ መጥቶ በቡናው ጨዋታ ከጫፍ ያደረሰው መከላከያ አሁን ያንን አቋም የማስቀጠል ግዴታ ይኖርበታል። በዚህም የሀዲያ ሆሳዕናን ወደ ቀኝ ያጋደለ ጥቃት መቋቋም እና ቀጥተኝነትን በቀላቀለ መንገድ ወደ ፊት ለመሄድ መሞከር ከቡድኑ የነገ የጨዋታ ዕቅድ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ለኳስ ቁጥጥር ጅርባ የማይሰጡ ዓይነት እንደመሆናቸው መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረውም ፍልሚያ ትኩረት ሳቢ ሊሆን ይችላል።
ይህ ጨዋታ በዮናስ ካሳሁን ዋና ዳኝነት ሲመራ ረዳቶቹ ሰለሞን ተስፋዬ እና ኤፍሬም ኃይለማሪያም አራተኛ ዳኛ ደግሞ ምስጋናው መላኩ በመሆን ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሆሳዕና እና መከላከያ እስካሁን ሦስት የሊግ ግንኙነት ታሪክ ሲኖራቸው አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው አንዴ ነጥብ ተጋርተዋል። ዕኩልነት በሰፈነበት ግንኙነታቸው ነብሮቹ 2 ጦሩ ደግሞ 3 ግቦች አሏቸው።
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)
ያሬድ በቀለ
ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሣ – ሔኖክ አርፌጮ
ብርሃኑ በቀለ – አበባየሁ ዮሐንስ – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ኢያሱ ታምሩ
ዑመድ ኡኩሪ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – ልደቱ ጌታቸው – ግሩም ሀጎስ
ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ
ተሾመ በላቸው – ቢኒያም በላይ – አዲሱ አቱላ
እስራኤል እሸቱ