ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም የመጀመሪያ በነበረው የረፋዱ ጨዋታ ላለመውረድ እየታተሩ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች አርባምንጭ ከተማን 2-1 በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበው ማንሰራራታቸውን ቀጥለዋል።

ጅማ አባ ጅፋሮች ባህር ዳር ከተማን ከረታው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ለዛሬ ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ወንድማገኝ ማርቆስ እና መሀመድ ኑር ናስር ወጥተው በምትካቸው ሽመልስ ተገኝ እና ዳዊት ፍቃዱን ያስገቡ ሲሆን በተቃራኒው በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጮች ደግሞ ግማሽ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸውን ቀይረው የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።

ኡቸና ማርቲን ፣ ሙና በቀለ ፣ አቡበከር ሻሚል ፣ ፍቃዱ መኮንን እና ሀቢብ ከማል ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርደው በምትካቸው አሸናፊ ፊዳ ፣ በርናርድ ኦቼንግ ፣ አሸናፊ ኤልያስ ፣ ኤሪክ ካፓዬቶ እና በላይ ገዛኸኝ በመጀመሪያ ተመራጭነት ገብተዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዶች ከተጫዋቾች ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ በመጀመረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋሮች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ ከኳስ ጀርባ ሆነው በመከላከል በቀጥተኛ ኳስ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በስፋት ሲንቀሳቀሱ ያስተዋልንበት አጋማሽ ነበር። 

በጨዋታው የመጀመሪያው ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በጅማ አባ ጅፋር በኩል ወደ ግራ እና ቀኝ ካደሉ የቆሙ ኳሶች እዮብ አለማየሁ እና አስጨናቂ ፀጋዬ ባደረጓቸው ሙከራዎች የተመዘገቡ ነበሩ። ነገር ግን ቀስ በቀስ በቀጥተኛ መንገድ መልሶ ማጥቃቶችን መሰንዘር የጀመሩ አርባምንጮች በዚህ ሂደትም በ29ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሆነዋል ፤ በላይ ገዛኸኝ ከራሱ ሜዳ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ አሸናፊ ኤልያስ በግሩም አጨራረስ አርባምንጭ ከተማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የአርባምንጭ ከተማ መሪነት ግን መዝለቅ የቻለው ለ5 ያክል ደቂቃዎች ነበር ፤ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የተሻማውን ኳስ አርባምንጮች መከላከል አለመቻላቸውን ተከትሎ አስጨናቂ ፀጋዬ ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብን ማስቆጠር ችሏል።

ክፍት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉበት ነበር ፤ በጅማ በኩል ሱራፌል ዐወል ከግራ መስመር አጥብቦ ከገባ በኋላ ወደ ግብ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም በአርባምንጭ በኩል ደግሞ ግብ አስቆጣሪው አሸናፊ ኤልያስ በጅማ ተጫዋቾች ስህተት መነሻነት ያልተጠቀማት አደገኛ ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ቅያሬዎችን በማድረግ የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች አጋማሹን በፈጣን ጥቃቶች ነበር የጀመሩት። በተለይም በዚህ ሂደት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን በ49ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት እንዲሁም በ57ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አራት የጅማ ተጫዋቾች አልፎ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው ከሁለተኛው የውሃ እረፍት ሲመልስ ግን ፍፁም ደካማ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ሳይጠበቁ በ76ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ከራሳቸው አጋማሽ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውን ሳምሶን አሰፋን አልፎ ባስቆጠራት ግሩም ግብ መሪ መሆን ችለዋል።

ከግቧ መልስ በነበሩት ደቂቃዎች ጅማዎች በጣም ተሻሽለው የተመለከትን ሲሆን በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ሆነ እንጂ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር በቻሉ ነበር። በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች በ84ኛው ደቂቃ ፍቃዱ መኮንን በግል ጥረቱ ካደረገው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ጥረት ሲያደርጉ ሳናስተውል ጨዋታው ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋሮች ነጥባቸውን ወደ 19 በማሳደግ በነበሩበት 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።