ሪፖርት | የአቡበከር ናስር ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን ባለድል አድርገዋል

ዘንድሮ በሊጉ የመጀመሪያ በነበረው የምሳ ሰዓት ጨዋታ አቡበከር ናስርን ከጉዳት መልስ ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በመከላከያ ያልተጠበቀ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ሮቤል ተ/ሚካኤል ፣ እንዳለ ደባልቄ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ ተመስገን ገ/ኪዳንን አስወጥተው በምተካቸው ኃይሌ ገ/ተንሳይ ፣ አብነት ደምሴ ፣ ዊልያም ሰለሞን ፣ አቡበከር ናስር እና ያብቃል ፈረጃን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።

በአንፃሩ ሰበታ ከተማን ረተው የመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ለዛሬው ጨዋታ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ያሲን ጀማል ፣ መጣባቸው ሙሉ ፣ አቤል አሰበ እና አቤል ከበደ ወጥተው በምትካቸው እንየው ካሳሁን ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ዳንኤል ደምሴ እና ሱራፌል ጌታቸውን በማስገባት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመርን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ ኢትዮጵያ ቡናዎች በራሳቸው ሜዳ ኳሶችን እንዲቀባበሉ በመፍቀድ በተወሰነ መልኩ ወደ መሀል ሜዳ አካባቢ ሲጠጉ ግን ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትንበት ነበር። በ12ኛው ደቂቃ ላይም በዛሬው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቡና መለያ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የጀመረው አብነት ደምሴ ወደ ኃላ የተመለሰን ኳስ ተረጋግቶ እንዳይቀበል ሱራፌል ጌታቸው ባሳደረው ጫና የነጠቁትን ኳስ ሄኖክ አየለ በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮ ድሬዳዋን ቀዳሚ ማድረግ መልሷል።

እምብዛም ኳስ ይዞ የመቆየት ፍላጎት ያልነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ፈጠን ባሉ ቅብብሎች በፍጥነት የኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉም እንዲሁ ተመልክተናል ፤ በተለይም በቀኝ እና በግራ የመስመር ተከላካዮቻቸው ፍጥነት በመጠቀም ኢትዮጵያ ቡናን ለመፈተን ጥረት ያደረጉ ሲሆን ወደ ሙከራነት አይቀየሩ እንጂ በተሻለ ወደ ቡና ሳጥን መድረስ ችለው ነበር።

በአጋማሹ ኳሶችን በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ከፍ ለማለት የተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ ውስን በሆኖ አጋጣሚዎች ነበር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሱት በዚህም በ24ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ኳስ በድሬዳዋ ሳጥን ከተቆጣጠረ በኋላ ከድሬዳዋ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ተጫዋች አልፎ ወደ ግብ የላካት ሙከራ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ። በ34ኛው ደቂቃ ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ከማዕዘን ምት በአጭር የጀመሩትን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ዳግም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የተመለሰው አቡበከር ናስር በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

ከግቧ በኋላ አጋማሹን በተሻለ መንገድ ማጠናቀቅ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በማጥቃቱ ረገድ መጠነኛ መሻሻሎችን አስመልክተውናል። በዚህም በተለይ በ42ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ በግሩም ሁኔታ ያሾለከለትን ኳስ አቡበከር ናስር አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት ኳስ እጅግ አስቆጭ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ከመጀመሪያው በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ53ኛው ደቂቃ ላይ ያብቃል ፈረጃ ያሻማውን ኳስ አውዱ ናፊዮ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተነሳ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር አስቆጥሮ ከመመራት ወደ መሪነት በመምጣት አጋማሹን ጀምረዋል።

ቀስ በቀስ የጨዋታ ቁጥጥራቸውን ማሳደግ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሶችን እየተቀባበሉ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በ59ኛው ደቂቃ ሄኖክ አየለ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ብሩክ ቃልቦሬ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ የግቡን ቋሚ ለትማ ከተመለሰችበት አጋጣሚ ውጪ የኢትዮጵያ ቡና ግብ ለመፈተሽ ተቸግረው ተስተውሏል።

ከውሃ ዕረፍት መልስ ግን በፈጣን ምልልሶችን ማስመልከት የጀመረው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። 

በድሬዳዋ ከተማ በኩል እንየው ካሳሁን እና ሙህዲን ሙሳ ያመከኗቸው በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ደግሞ አቡበከር ናስር በሦስት አጋጣሚዎች ያመከናቸው ኳሶች እጅግ አደገኛ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 31 በማሳደግ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በአንፃሩ በነበሩበት 24 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ያጋሩ