የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-1 ድሬዳዋ ከተማ

ቀትር ላይ የተካሄደውን ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለውጤቱ ከጫና የመውጣት አስተዋፆኦ

” ሁሌም እንደምለው ነው። በየጨዋታው ጫናው ሁሌም የሚቀጥል ነው። ልጆቻችንንም በሥነ ልቦና እያዘጋጀን ሥራችንን መስራት ነው። ጫናው ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል። እኛም ፣ ደጋፊውም ማሸነፍ የሚፈልገው ነገር ነው። ሁልጊዜ እኛ ጋር ተጫዋቾቻችን ጋር ያለው ጫና ከደጋፊው ስለመጣ ስላልመጣ ሳይሆን ውጤት ባጣን ቁጥር ያንን መልሰን ለማግኘት ሜዳ ውስጥ የሚፈለገውን ጥንቃቄዎች የመሳሰሉ ነገሮች፣ አንዳንድ ጊዜ መስመሩን ሲያልፍ የሆነ ፍርሀት ይመጣል። ያ ደግሞ ጨዋታችንን ያበላሽብናል። በተቻለ መጠን ያ እንዳይሆን የተጫዋቾቻችንን ሥነ ልቦና ማዘጋጀት ነው። የውጤቱ መምጣት ጥሩ ነው። የሚያግዝ ነገር ስለሞኖረው።

በጨዋታው ስለወሰዱት እርምት

” አዎ በተለይ የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ቀድሞ ነበር ጎል የተቆጠረብን። ግን ጎል በማግባት ሂደት ውስጥ ተጋጣሚን የምንቆጣጠርበትን አጨዋወታችንን እንዳንለቅ ነው። በዛ ውስጥ እንግዲህ የሚቋረጡ፣ የሚበላሹ ኳሶች ይኖራሉ። ግን ሁል ጊዜ የምናየው ሂደቱን ማስቀጠል እንዲቻል ዕድሉ ነበር ወይ? ለምድነው የተበላሸው ዕድሉ ? ከሌለ እንቅስቃሴውን የማደርግ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ዕድሉ ካለ ግን ተጫዋቹን የማረም ጉዳይ ነው። እዛ ውስጥ የቆየንበት ጉዳይ ነው ብዬ የማስበው።

ስለሜዳው ምቾት?

“ጥሩ ነው። ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ ጥሩ ነው። በነገራችን ላይ ሜዳ ለሁሉም ነው። የተለያየ አቅም፣ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች ስላሉ ብቃታቸውን ለማሳየት ሜዳው ወሳኝ ነው። በደንብ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ያለ ሜዳ ውድድር ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ሜዳው በተወሰነ እኛንም እነርሱንም አግዞናል ብዬ አምናለው።”

አሰልጣኝ ሳምሶም አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ጨዋታው በፈለጉት መንገድ ስለመሄዱ

“አይደለም። ሁለቱም አርባ አምስት ላይ በዛ ልክ አልሄደም። ስህተቶች ነበሩበት ተረጋግተን ኳስ ይዘን መጫወት አልቻልንም። በተለይ ቀድመን ጎል ከማግባታችን ጋር ተያይዞ እሱን የማስጠበቅ ወደ ኋላ የማፈግፈግ ሁኔታዎች ነበሩ። የኳሶቹ አካሄድ በጣም የተቆራረጡ ነበር ፤ ወጥ አልነበሩም። ሰዎችም ስንቀይር በተመሳሳይ ነው የነበረው። እንግዲህ ያለንበት ቀጠና የፈጠረው ነው። ምናልባት ዛሬ ውጤታችንን አስጠብቀን ብንወጣ ኖሮ ከዚህኛው ቀጠና በጣም ሸሽተን ወደ አስተማማኝ የምንሄድበት ነበር። ዞሮ ዞሮ በርካታ ቀሪ ጨዋታዎች ስላሉ ጠንክረን እንሰራለን።

ስለተጫዋች ቅያሪ

“ለውጥ አላመጡም። እርሱ ነው አንዱ ክፍተታችን ያለፉት ሁለት ሦስት ጨዋታ ላይ ተቀይረው የሚገቡ ልጆች ተፅዕኗቸው ቀጥተኛ ነበር። ዛሬ የገቡት ልጆች ግን ይህ ነው የሚባል ነገር የለም። በቀጣይ ይህን እያረምን ጠንክረን እንቀርባለን።”

ያጋሩ