የአዳማውን ውድድር በድል የተሰናበተው መከላከያ የባህር ዳር ቆይታውንም ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በመርታት ጀምሯል።
መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡናው ድል መልስ ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ ክሌመንት ቦዬን ተክቶ እንዲሰለፍ ሲያደርግ አሌክስ ተሰማ እና ዳዊት ማሞም ጉዳት ባገኛቸው አሚን ነስሩ እና ገናናው ረጋሳ ምትክ ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ መጥተዋል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ከአዲስ አበባው አቻ በአበባየሁ ዮሐንስ ቦታ ኤፍሬም ዘካሪያስን ተክተዋል።
በጥሩ ፉክክር በጀመረው ጨዋታ ቡድኖቹ የመጠናናት ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲቆዩ መከላከያዎች በጊዜ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። 9ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች መሀል ላይ ካቋረጡት ኳስ ምንተስኖት አዳነ ያስጀመረውን ጥቃት ቢኒያም በላይ ጊዜውን የጠበቀ ልዩ ኳስ አመቻችቶለት እስራኤል እሸቱ በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።
መከላከያዎች ከግቡ በኋላም ፈጣን ጥቃታቸው በድጋሚ ወደ ግብ ሲያቀርባቸው 12ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ከቀኝ ወደ ሳጥን ውስጥ ክሮስ ያደረገውን አዲሱ አቱላ በግማሽ ቮሊ ሞክሮ ወደላይ ወጥቶበታል። በቀጣዩ ደቂቃ ግን የአጋማሹ ትኩረት ሳቢ ክስተት ተፈጥሯል። በዚህም ወደ መከላከያ ሳጥን የተጣለውን ረጅም ኳስ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ኢብራሁም ሁሴን እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ከባድ ግጭት ገጥሟቸው ኢብራሂም ተቀይሮ በልደቱ ጌታቸው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
ይህ እና ሌሎች ግጭቶች ጨዋታውን ቀዝቅዘ አድርገውት ሲቀጥል ሆሳዕናዎች በሂደት ኳስ መስርተው ጫና ለመፍጠር ጥረታቸውን ቀጥለዋል። የጦሩ ተጫዋቾችም ወደ ግባቸው በመጠጋት በጥልቀት በመከላከል እንዲሁም ወሳኝ ቦታዎች ላይ በመገኘት የሆሳዕናን ቅብብሎች በማቋረጡ ገፍተውበታል። ነብሮቹ ለግብ በቀረቡበት አጋጣሚ 30ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ በድንቅ ኳስ ዐመድን ከግብ ጠባቂው ጋር ቢያገኛውም ሙሴ የዑመድን ሙከራ አምክኗል። በቀሪ ደቂቃዎችም ነብሮቹ ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለው የመከላከያን አጥር አልፈው ግብ አፋፍ የደረሱባቸውን ከሦስት ያላነሱ አጋጣሚዎችን ግብ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቅያሪ በማድረግ ቅርፃቸውን ወደ 4-3-3 በማምጣት ይበልጥ አጥቅተው ለመጫወት ሲገቡ መከላከያዎች በበኩላቸው የአማካይ ክፍላቸውን ቁጥር ከፍ በማድረግ ለተጋጣሚያቸው ጥቃት ምላሽ መስጠትን መርጠዋል። ሆኖም ነብሮቹ ወደሚፈልጉት የማጥቃት ጫና ሪትም ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ጦሩ ሌላ ግብ አክሏል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ የነበረው ቢኒያም በላይ ከኤሌክስ ተሰማ ግንባር የደረሰውን ኳስ ከግራ መስመር ሲያሻግር አዲሱ አቱላ በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ በኋላም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዕድሎችን ለመፍጠር ከመሞከር አልቦዘኑም። 58ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዘካሪያስ ሳጥን ውስጥ ዳዊት ማሞን በድንቅ ሁኔታ አልፎ ግልፅ ዕድል ቢያገኝም ለሙሴ ከባድ የሆነ ሙከራ ማድረግ አልቻለም። 65ኛው ደቂቃ ላይም ፍቅረየሱስ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ነበር የወጣው። ቡድኑ በቅብብሎች ለመግባት ጥረቱን አጠናክሮ ሲቀጥል አማካዮቹ በጦሩ ሳጥን መግቢያ ላይ በማራኪ ሁኔታ በነካኩት እና ተቀይሮ የገባው አበባየሁ ዮሐንስ በድንቅ ሁኔታ ያመቻቸውን ሀብታሙ ታደሰ 76ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎት ልዩነቱን አጥብቧል።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ነብሮቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ማጥቃቱ አተኩረው በእንቅስቃሴ እና በቆሙ ካሶች ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም በተመኙት መልኩ የግብ ዕድሎችን አላገኙም። ይልቁኑም ውጤታቸውን ለማስጠበቅ የተፋለሙት መከላከያዎች ተቀያሪዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ ናቢ ሰይላ እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ ዮሐንስ መንግሥቱ በመልሶ ማጥቃት ንፁህ ዕድል አግኝተው አምክነዋል። ሆኖም ግን ውጤቱን አስጠብቆ መጨረስ አልተሳናቸውም።
በ2-1 ውጤቱ ተከታታይ ድል ያሳካው መከላከያ ነጥቡን 27 አድርሶ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል 29 ነጥቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና 7ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።