መከላከያ ተከታታይ ድሉን ሀድያ ሆሳዕናን በማሸነፍ ካሳካበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ረዳት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ – መከላከያ
ስለ ዛሬው ተከታታይ ድል
“በዚህም በዛም አሸንፈናል፡፡ አንዳንዴ በፈለከው መንገድ አይሆንልህም፡፡ በእርግጥ ሀድያም ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ጥሩ ስብስብ ያለው ነው፡፡ ከሞላ ጎደል የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል ብዬ ነው የማስበው ፤ ሦስት ነጥብ ነው የፈለግነው። ስለዚህ ዛሬ ደግሞ በጣም ብዙ ክፍተቶች ያየንባቸውን ለሚቀጥለው ጨዋታ የተሻለ አድርገን እንመጣለን፡። ምክንያቱም እየከበደ ነው የሚሄደው፡፡ የሚከብዱንን ነገሮች እንዴት አቅልለን ሦስት ነጥብ ማግኘት እንዳለብን ጥረት እናደርጋለን፡፡ የዛሬው ሦስት ነጥብ ይበልጥ እኛን ሊያነሳሳ ይችላል ብዬ አስባለሁ ፤ ተመስገን፡፡
2-0 ከመሩ በኋላ ስለነበራቸው እንቅስቃሴ
“ካገባህ በኋላ ከእንደገና ጨዋታውን እየተቆጣጠርክ ለማግባት የምታደርገው ጥረት ደግሞ የተጫዋቾችህ ኳሊቲ እና ሜዳ ውስጥ ባሉት ልጆች ነው የሚወሰነው፡፡ ስለዚህ ግማሹ ለማጥቃት ግማሹ ለመከላከል ከሆነ ችግር ነው፡፡ በቀጣይ አግብተንም እንደዚህ ዓይነት ነገር ሊያጋጥመን ስለሚችል ምንድን ነው የምናደርገው የሚለውን ነገር በቀጣይ በደንብ ልንሰራበት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀድያ ሆሳዕና
ስለ ጨዋታው
“እንደተመለከታችሁት ቆንጆ ነበር፡፡ በራሳችን ጥቃቅን ስህተቶች ነው ዛሬ የተሸነፍነው፡፡ ግን ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡
መጀመሪያ ላይ ጎል ስለማስተናገድ እና ቀድሞ ጎል ያለማስቆጠር ችግር
“አንዳንድ ጊዜ እንደ ከተማም እንደ አጀማመራችንም ትንሽ መዘናጋቶች ነበሩ፡፡ ሁለት ሦስት ጨዋታዎች ላይ አሁንም እንደዛ ነበር፡፡ እስከ ዘጠና ደቂቃ ድረስ ልጆቹ ብዙ ሙከራ አድርገዋል፡፡ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ይቺን ልናስተካክል እና ፊኒሺንግም ነው የሚቀረን እንጂ ቡድኑ በአጠቃላይ ጥሩ ነበር እስከ መጨረሻ፡፡ ስገባ እንዳልኩት ተጋጣሚዎቻችን ከባዶች ናቸው፡፡ ያሉበትም ቦታ ጥሩ ስላልሆነ የዚህ ዓይነት ቻሌንጅ እንደሚገጥመን እናውቅ ነበር፡፡