ቅድመ ዳሰሳ | የ22ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የነገ ሦስት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።ፊ

ሰበታ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ከሽንፈት መልስ የሚገናኙት ሰበታ እና ሀዋሳ ባሉበት የፉክክር ደረጃ ውስጥ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር እየተራራቁ ይገኛሉ። ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ሰበታ ከተማዎች በየሳምንቱ ነጥብ ይዘው በመውጣት ላይ ከሚገኙት ጅማ ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አንፃር ሲታዩ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይበልጥ ለመውረድ አደጋ ተቃርበው ይታያሉ። ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገኙት ሀዋሳ ከተማም እንዲሁ ከሁለተኝነት ደረጃው እንኳን በአራት ነጥቦች ለመራቅ ተገዷል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ በዙሪያቸው ካሉ ቡድኖች ጋር ተጨማሪ ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል።

ሰበታ ከተማ አሁንም በእንቅስቃሴ ረገድ ተስፋ እየሰጠ ውጤት ማስመዝገብ ላይ ግን እንደተቸገረ ቀጥሏል። የኳስ ቁጥጥርን ዋነኛ የግብ ዕድል መፍጠሪያ መንገዱ አድርጎ የሚከተለው ሰበታ በቅብብሎች ሰብሮ ለመግባት ብዙ ሲቸገር መግባት በቻለባቸው አጋጣሚዎችም መጨረስ እየተሳነው ከኋላ የሚተወው ክፍተትም ለጥቃት ሲያጋልጠው በቅርብ ጨዋታዎች ስንታዘብ ቆይተናል። የነገ ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማም ከተከላካይ መስመር ጀርባ በፈጣን ሽግግር ለመግባት የሚያስችል መዋቅር ያለው በመሆኑ ሰበታ በያዘው የኳስ ቁጥጥር መንገድ ይበልጥ ጥራት ጨምሮ የመምጣት ግዴታ ውስጥ ይገኛል።

ሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመባቸው ጨዋታዎች ለሀዋሳ ከተማ ቀላል አልነበሩም። ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በተጨማሪ ቡድኑ ባልተረጋጋ የተከላካይ መስመር ስድስት ግቦችን ማስተናገዱ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነበር። እርግጥ የነገ ተጋጣሚው ማጥቃት ደካማ ሆኖ የከረመ ከመሆኑ አንፃር ይህ የኋላ ክፍል ችግሩ ላይጋለጥ ቢችልም ከስህተት የፀዳ ዘጠና ደቂቃ እንደሚያሳልፍ በእርግጠኝነት መናገር ግን አይቻልም። ወደ ፊት የሚሄድበት የጨዋታ ዕቅድ ግን ሙሉ ለሙሉ ለሰበታ የኳስ ቁጥጥሩን ባይለቅም መሀል ላይ በሚያቋርጣቸው ኳሶች መነሻነት ሁለቱን መስመሮች በተለይም የግራውን ወገን ያማከሉ ፈጣን ጥቃቶች ላይ የሚመሰረት እንዲሆን ይጠበቃል።

ሰበታ ከተማ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከጉዳት ሲመለሱለት ምንተስኖት ዓሎን በጉዳት ፍፁም ገብረማሪያምን ደግሞ በቤተሰብ ጉዳይ ምክንያት ያጣል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ጨዋታው በእያሱ ፈንቴ ዋና ዳኝነት ሲመራ
ማንደፍሮ አበበ እና አያሌው አሰፋ ረዳቶች
ዓለማየሁ ለገሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበውበታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ከዚህ ቀደም በዘጠኝ አጋጣሚዎች እርስ በእርስ ሲገናኙ ሰበታ ከተማ አምስቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በጨዋታዎቹ ሰበታ ከተማ 11 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 9 ግቦች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ዴሪክ ኒስባምቢ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

ዳግም ተፈራ

ካሎንጂ ሞንዲያ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – ዮሐንስ ሴጌቦ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ተባረክ ሄፋሞ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

በአስር ነጥቦች ሊጉን መምራቱን የቀጠለው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ያለሽንፈት ጉዞውን ቀጥሏል። ይህንን የመሪነት ልዩነት ባለበት ለማስቀጠል አልያም ለማስፋት ሁሉንም ጨዋታዎች በእኩል መመልከት አስፈላጊው በመሆኑም ከነገው ጨዋታም ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ያልማል። አዳማ ከተማ በበኩሉ ከተጋጣሚው በላይ ነጥቦቹ እጅግ የሚያስፈልጉት ጊዜ ላይ ይገኛል። በመቀመጫ ከተማው ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ብቻ ያሳካው አዳማ ሳይታሰብ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ካሉ ክለቦች ጋር ነጥቡ እየተቀራረበ በመሆኑ በቶሎ ከድል ጋር ተገናኝቶ በአስተማማኝ የነጥብ ርቀት ላይ መቀመጥ ያስፈልገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመከላከያው የአቻ ውጤት በኋላ ቀጥተኛ ተፎካካሪዎቻቸው የሆኑት ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን የረቱበት መንገድ ምን ያህል ለውጤት የተሰራ ስብስብ እየገነቡ እንደሆነ ያሳየ ነበር። በጨዋታዎቹም ያን ያህል የእንቅስቃሴ ብልጫ ሳይወስዱ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ያሳኩበትን ሂደት ነገም እንደሚደግሙ ይጠበቃል። የሊጉ ሁለተኛው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆነው አዳማ ከተማን መግጠማቸው ግን ፈተናቸውን እንደሚያበዛ እና ነገሮች ቀላል እንደማይሆኑላቸው እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ይህንን ተከትሎ ቀጥተኝነት አጨዋወቱን በደንብ ለመጠቀም እንደሚጥር የሚታሰበው ስብስቡ ዕድሎችን በክፍት ጨዋታ በተደጋጋሚ ለመፍጠር ባይችልም የቆሙ ኳሶችን እንደ ግብ ምንጭነት ሊጠቀም ይችላል። ከዚህ ውጪ ፈጣኖቹ አጥቂዎች ከተከላካይ ጀርባ እየተገኙ የሚከውኑት ስራ ለቡድኑ አንዳች ነገር ሊያስገኝ ይችላል።

አዳማ ከተማ ጠንካራ ጎኑ ከሆነው የመከላከል አደረጃጀት አንፃር በነገው ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ የወሰዱት መከላከያ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ዓይነት አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ምናልባት ከእነዚህ ቡድንኖች በተለየ እንደአስፈላጊነቱ ከኳስ ጋር ለመቆየት ቢሞክር እንኳን ከኳስ ውጪ ግን በቶሎ ወደ መከላከል ቅርፁ የሚመለስ እንዲሁም ከግብ ክልሉ ሳይርቅ የሚከላከያ አዳማ ነገ ይጠበቃል። ቡድኑ ለአየር ላይ ኳሶች ምቹ የሆኑ ተከላካዮችን የያዘ እንደመሆኑ ተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶችን በትኩረት መከላከል እንዲሁም የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ኃላፊነት ቀንሶ የጊዮርጊስን የኮሪደር እንቅስቃሴ መዝጋት ላይ ሊያተኩር ይችላል። በዚህ ውስጥ ግን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም ጠንካራውን የቅዱስ ጊዮርጊስን የኋላ ክፍል ለማለፍ ፊት ላይ በቁጥር በርክቶ በማጥቃቱ ረገድ ውስንነት ሊኖርበት ይችላል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ እና አዲስ ግዳይን በጉዳት ጋቶች ፓኖምን በቅጣት ሲያጣ አቤል ያለው ከጉዳት አገግሞ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና ሱሌማን ሀሚድ ቅጣታቸውን ጨርሰው ይመለሱለታል። አዳማ ከተማም በበከሉ አጥቂው ዳዋ ሆቴሳን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ግብ ጠባቂው ሴኩምባ ካማራም ቡድኑን መቀላቀሉ ተሰምቷል።

ለሚ ንጉሴ ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት በረዳትነትን ድሪባ ንጉሴ እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ እንዲሁም በ4ኛ ዳኝነት ደግሞ አሸብር ሰቦቃ ተሰይመዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 39 ጊዜያት የተገኛኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀያውን በማሸነፍ የተሻለ ሪከርድ ይዟል። አዳማ ከተማ በአንፃሩ ሰባት ጊዜ ሲረታ 12 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸውም ጊዮርጊስ 51 አዳማ ከተማ ደግሞ 26 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – የአብስራ ተስፋዬ

አቤል ያለው – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ

አማኑኤል ገብረሚካኤል

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – ሚሊዮን ሰለሞን – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ

ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከድል ጋር ከተራራቁ ሰንበትበት ብለዋል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ወላይታ ድቻ ሙሉ ሦስት ነጥብ ካሳካ አምስት ጨዋታዎች ያለፉ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ደግሞ የወልቂጤውን የፎርፌ ውጤት ሳይጨምት ለመጨረሻ ጊዜ ድል የቀናው ከስምንት ሳምንታት በፊት ነበር። የነገው ጨዋታ ለወላይታ ድቻዎች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ ጋር በነጥብ የመስተካከል ዕድልን ሲፈጥርላቸው ከወራጅ ቀጠናው አራት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ደግሞ በመቀመጫ ከተማው የሚያደርገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ፈቀቅ ያደርገዋል።

ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው ሳምንት ቀጥተኛ ተፎካካሪው ፋሲል ከነማን አንድ ለምንም እየመራ በሁለተኛው አጋማሽ እጅ የሰጠበት መንገድ ቡድኑ ለዋንጫ የተራበ እንዳልሆነ ብዙዎችን እንዲጠራጠሩ አድርጓል። ለወትሮ የሚፈልገውን ካገኘ በኋላ ችምችም ብሎ ግቡን ላለማስደፈር የሚታትረው ስብስቡ በጠቀስነው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ክፍተቶችን ለፋሲል ተጫዋቾች ሲሰጥ የነበረበት መንገድ እጅ እንዲሰጥ አድርጎታል። በነገው ጨዋታም በመስመሮች መካከል እና ከተከላካይ ጀርባ የሚተው ቦታዎች ከኖሩት መቀጣቱ አይቀሬ ነው። በተቃራኒው በማጥቃቱ ረገድ ደግሞ ፈጣን ሽግግሮችን እና ረጃጅም ኳሶችን በመላክ ግብ ለማግኘት እንደሚንቀሳቀስ ቀድሞ መናገር ይቻላል።

በባህር ዳር 21ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ላለመውረድ እየተጣጣረ በሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የተረታበት መንገድ ያልተጠበቀ ነበር። ከሁሉም በላይ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች የተቆጠሩበት ተመሳሳይ የቆሙ ኳሶች ግቦች የቡድኑን ወቅታዊ ችግር የሚያሳዩ ይመስላል። ይህ የቀጠና እና የሰው ለሰው አያያዝ የመከላከል አጨዋወት ነገ ካልተስተካከለ ደግሞ በተቃራኒው ጠንካራ ጎናቸው በሆነው ወላይታ ድቻዎች መፈተኑ አይቀሬ ነው። በማጥቃቱ በኩል ተለምዷዊው ፍፁም ዓለሙን ያማከለ አጨዋወት ነገም እንደሚቀጥል ሲጠበቅ ከኳስ ጀርባ ሆነው እንደሚጫወቱ የሚገመቱትን የድቻ ተከላካዮች ለመዘርዘርም ተደጋጋሚ የመስመር ላይ ሩጫዎች በመስመር አማካዮች እና ተከላካዮች እንደሚዘወተር ይጠበቃል።

ሁለቱም ተጋጣሚዎች ዋነኛ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቻቸውን የሚያጡ ሲሆን የወላይታ ድቻው ስንታየሁ መንግስቱ በጉዳት የባህር ዳር ከተማው ኦሴይ ማዉሊ ደግሞ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ናቸው።

ኤፍሬም ደበሌ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ክንዴ ሙሴ እና ሸዋንግዛው ይልማ ረዳት ዳኞች ባህሩ ተካ ደግሞ 4ኛ ዳኛ ናቸው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ እስካሁን በሊጉ በአምስት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል። በሦስቱ ግንኙነታቸውን አቻ ሲለያዩ አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል። በጨዋታዎቹ እኩል አምስት አምስት ግቦችንም አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

ያሬድ ዳዊት – ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – ሔኖክ ኢሳይያስ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አብዱልከሪም ኒኪማ

ተመስገን ደረሰ – ዓሊ ሱሌይማን – ግርማ ዲሳሳ

ያጋሩ