በዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች በሁለቱ አጋማሽ የነበራቸውን የበላይነት በግብ ማጀብ ባለመቻላቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ባደረጓቸው አምስት ለውጦች ምንተስኖት አሎ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ቢያድግልኝ ኤሌያስ ፣ ታፈሰ ሰርካ እና ዱሬሳ ሹቢሳ ወጥተው በምትካቸው ለዓለም ብርሃኑ ፣ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ በረከት ሳሙኤል እና ቢስማርክ አፒያን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሲያስጀምሩ በአንፃሩ የዘርዓይ ሙሉው ሀዋሳ ከተማ በበኩል በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረታው ስብስብ ላይ የአራት ተጫዋቾች ለውጦችን አድርጓል። በዚህም ወንድማገኝ ሀይሉ ፣ መድሀኔ ብርሃኔ ፣ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ወጥተው በምትካቸው ፀጋአብ ዮሀንስ ፣ አቤኔዘር ኦቴ ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ኤፍሬም አሻሞ በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊ በመሆን ጀምረዋል።
ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሰበታ ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነት ነበራቸው። በተለይም ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል ፤ በዚህ ሂደት ጌቱ ሃይለማርያም እና ሳሙኤል ሳሊሶ የተሰለፉበት የቡድኑ የቀኝ መስመር ማጥቃት ሀዋሳ ላይ ተደጋጋሚ አደጋዎችን ሲደቅን አስተውለናል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ቢስማርክ አፒያ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ያመከናት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከተደረጉት ሙከራዎች እጅግ አደገኛዋ አጋጣሚ ነበረች።
በርከት ያሉ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት ሳይዙ ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ፍፁም ደካማ የጨዋታ አጋማሽን አሳልፈዋል። በ23ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ በግንባሩ ገጭቶ ከሞከራት ኳስ ውጪ በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹን ፈፅመዋል።
ከውሃ ዕረፍት በፊት በቀኝ በኩል አመዝኖ የነበረው የሰበታ ከተማዎች ማጥቃት ከውሃ ዕረፍት መልስ ደግሞ ወደ ግራ አድልቶ የተመለከትንበት ነበር። በዚህም ከግራ መነሻቸውን ያደረጉ ጥቃቶች ቁጥርም አይሎ ተመለክተናል። በተለይም በ32ኛው ደቂቃ ዴሪክ ኒሲምባቢ ከግራ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ የመታው እና ዳግም ተፈራ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች። በጨዋታው በሀዋሳ ከተማ አጋማሽ በርከት ያሉ ቅብብሎችን ማድረግ የቻሉት ሰበታዎች ይህን ሂደት ወደ ጥራት ያላቸው ዕድሎች በመቀየር ረገድ ውስንነት ነበረባቸው።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በተመሳሳይ ጨዋታውን ወደ ተጋጣሚ አጋማሽ በመውሰድ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የሀዋሳን ሳጥን መጎብኘት የጀመሩት ሰበታዎች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአጋማሹ ፍፁም የሆነ የበላይነት የነበራቸው ሰበታ ከተማዎች ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በ73ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ያሻሙትን ኳስ ሀዋሳዎች በአግባቡ መከላከል አለመቻሉን ተከትሎ ሳጥን ውስጥ ያገኙትን ኳስ ጌቱ ሃይለማርያም በግራ እግር የሞከራትን እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ከገባ በኋላ ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ የላከውንም ኳስ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ በግሩም ቅልጥፍና ያዳነባቸው ኳሶች አደገኛ ነበሩ። በ84ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ጌቱ ሃይለማርያም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ድንቅ ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ በግንባሩ ሸርፎ የሞከራት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታበታለች።
በሁለተኛው አጋማሽ ወንድማገኝ ኃይሉን ቀይረው በማስገባት ራሳቸውን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ ፍፁም ደካማ ነበሩ። ምስጋና ለግብ ጠባቂያቸው ይግባ እንጂ እንደነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በጨዋታው ነጥብ ሳያገኙ በወጡ ነበር።
ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማዎች በ14 ነጥብ አሁንም በሊጉ ግርጌ ሲገኙ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ35 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።