የረፋዱ ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ብርሀኑ ደበሌ – ሰበታ ከተማ
ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ
“ያው እንዳያችሁት ነው። ጨዋታው ውጥረት የተሞላበት ነው። ጎል ለማግባት ከነበረን ጉጉት በርካታ ኳሶችን አምክነናል። ለዚህም ዋጋ ከፍለን አቻ ወጥተን ጨርሰናል። የእግርኳስ ባህሪው ነው።
ስለአገኙት አጋጣሚ ያለመጠቀም
“አንዳንድ ጊዜ ፍፁም ያለመረጋጋት ነገሮች ልጆቹ ላይ ይታይባቸው ነበር። ጎል አስቆጥረው ለማሸነፍ ከነበራቸው ጉጉት የመነጨ ነው ብዬ የማስበው።
የሰበታ በሊጉ የመቆየት ጥርጣሬ
“ ከ27 ነጥብ 24 ነጥብ ይቀራል። በእግርኳስ የሚሆነው ነገር ስለማይታወቅ የግድ መልፋት ፣ መስራት ፣ መድከም ያስፈልጋል። የሚሆነው እስኪሆን ድረስ እንጂ ያለቀለት ነው ብዬ አላስብም።”
አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው እንቅስቃሴ
“አስቸጋሪ ነው። ሰባት ልጅ ከቋሚ ተሰላፊ ውስጥ ስታጣ አጨዋወትህንም ትቀይራለህ ፤ ስንከላከል ነበር። ባገኘነው ነበር ለመሄድ ያሰብነው። ዛሬ ወደፊትም አልሄድንም ፣ ሙከራም አላደረግንም። ስንከላከል ነው የዋልነው። አቻ ለእኛ ትልቅ ውጤት ነው። ምክንያቱም ባደረግነው እንቅስቃሴ ሰበታ የተሻለ ነበር።
በጨዋታው ስለበዙ ጥፋቶች
“ያው አንዳንዴ አቅምህን ስትጨርስ ጥፋቶች ይታያሉ። በቀጣይ ግን በቅጣት ፣ በጉዳት የወጡ ልጆች ይመለሳሉ። አንዳንዴ ድካም ሲኖር ሚፈጠር፣ የሚከሰት ነው። እየተካካን ለማስቀጠል እንሞክራለን።”