ሪፖርት | ፈረሰኞቹ በአዳማ ተፈትነው አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ጠንከር ያለ ፈተና ቢገጥመውም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረች ግብ ውጤት አስጠብቆ በመውጣት ነጥቡን 50 አድርሷል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሀዋሳ ከተማን ከረታው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ጋቶች ፖኖም እና አዲስ ግደይን አስወጥተው በምትካቸው ናትናኤል ዘለቀ እና ሀይደር ሸረፋን ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡድን የሥስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ጀማል ጣሰው ፣ ቶማስ ስምረቱ እና አብዲሳ ጀማል ወጥተው በምትካቸው ሴኮቡ ካማራ ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና ዳዋ ሆቴሳ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ገብተዋል።

ጨዋታው ገና በማለዳ ነበር የመጀመሪያ ግቡን ያገኘው። በ3ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻሙትን የቅጣት ምት ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል የመጀመሪያውን ኳስ ሲያሸንፍ በሩቁ ቋሚ የነበረው ከነዓን ማርክነህ ኳሷን በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

በተቆጠረባቸው ግብ እምብዛም ያልተረበሹት አዳማ ከተማዎች በእርጋታ ኳሶችን በመቀባበል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ብርቱ ጥረት አድስገዋል። በአውንታዊነት መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበን በአደገኛ ስፍራ የነጠቀውን ኳስ አሜ መሀመድ የተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው አቡበከር ወንድሙ ያቀበለውን አቡበከር ወደ ግብ ቢልክም ቻርልስ ሉክዋጎ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት አጋጣሚ አቻ ሊሆኑ የሚችሉባት ነበረች።

በአንፃሩ በአጋማሹ አዳማዎች ለማጥቃት በማሰብ ወደ ጊዮርጊስ አጋማሹ በሚጠጉበት ወቅት በሚቋረጡ ኳሶች ከተከላካይ ጀርባ የሚኖረውን ክፍተት በቀጥተኛ ኳስ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም በ31ኛው ደቂቃ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ ወደ ፊት የላከውን ኳስ ተጠቅሞ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሊያስቆጥር ሲል አዲስ ተስፋዬ ያዳነበት ኳስ የዚህ ሂደት ማሳያ አጋጣሚ ነበረች። በተጨማሪም በ33ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ሄኖክ አዱኛ ያሻውን ኳስ ደስታ ደሙ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ የገጨውን እንዲሁ ሴኩባ ካማራ አድኖበታል።

በአጋማሹ የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃዎች ከፍተኛ ጫና አሳድረው መንቀሳቀስ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ40ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ ቻርልስ ሉኩዋጎ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ የተፈጠረውን አጋጣሚ አሜ መሀመድ ተረጋግቶ ማስቆጠር የሚችለውን ከግቡ አናት በላይ ሰዷታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅምሩ ካቆሙበት የቀጠሉት አዳማዎች በቅብብሎች በፍጥነት ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር። በ55ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም በ63ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ዳዋ ከግቡ ትይዩ የሞከረው እና ለጥቂት ወደ ውጪ ከወጣበት የቅጣት ምት ኳስ ውጪ ቡድኑ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን ከመጠጋት በዘለለ ጥሩ መከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በጨዋታው በመሀል ሜዳው ፍልሚያ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የተወሰደባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጥልቀት ከመከላከል ባለፈ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ወቅት ያላቸው የመልሶ ማጥቃት አፈፃፀምም እንደ ወትሮው አመርቂ አልነበረም።

በአጋማሹ በ80ኛው እና 91ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊ አርአያ ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር በግሩም ቅብብል ሳጥን ውስጥ ደርሰው ያደረጓቸው ሁለት ሙከራዎች በካማራ እና የአዳማ ተከላካዮች ርብርብ ከመከኑባቸው አጋጣሚ ውጪ ፍፁም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተወሰደባቸው አጋማሽ ተቸግረው አስተውለናል። ሆኖም ግን ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት ተሳክቶላቸው 1-0 መርታት ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ነጥባቸውን ወደ 50 በማሳደግ በርቀት ሊጉን መምራታቸውን ሲቀጥሉ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ26 ነጥብ ወደ 10ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።

ያጋሩ