ፈረሰኞቹ ካሸነፉበት የ07:00 ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለጨዋታው ክብደት
“ በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር። ገና ስንጀምር ተናግሬያለሁ ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን። ሁሌም በከባድ ጨዋታ ውስጥ ሆኖ እንደዚህ ያለ ውጤት ይዞ መውጣት ትልቅ ነገር ነው።
ወደ ኋላ ስለማፈግፈጋቸው
“አንደኛ ሜዳው ላይ የመጀመርያ ጨዋታችን ነው። የሜዳውን እንቅስቃሴ ፣ አንዳንድ ነገሮች ሊቸግረን ይችላል። ጎል አግብተናል ይሄን እየጠበቅን ቶሎ ማጥቃት ይጠበቅብናል ፤ እንደዛ ነው ያደረግነው። አዳማ ጥሩ ቡድን ነው ፤ ኳሱን ይጫወታል። እኛም እየተጫወትን ሸሽተን አይደለም። ጨዋታውን ባላንስ እያደረግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመሄድ ነበር። ይሄንንም አድርገናል። በሁለተኛው አጋማሽ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ሦስት የጎል አጋጣሚዎች አግኝተናል። አልተጠቀምንም እግርኳስ ይሄ ነው። የተሻለ ነገር አድርገን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል።
ስለዋንጫው ጉዞ
“ይሄ አይደለም ፤ አሁንም ነገም ከፊት ያሉብንን ጨዋታዎች እያሰብን ነው የምንሄደው። የመጨረሻውን ግብዓት የምናገኘው በመጨረሻው ጨዋታ ነው። አሁን ከፊታችን በነጥብ የሚቀርበን ከባድ ጨዋታ አለብን። የተሻለ ነገር ሰርተን ጥሩ ነገር ለማምጣት ነው የምንሄደው።”
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ብናገኝ ትክክል ይሆን ነበር። ባሰብነው መንገድ ኳሱን ተቆጣጥረን እስከ መጨረሻው ጨዋታው ሄዷል። ወደ እነርሱ ወደ ሜዳ ክፍል በመሄድ የጎል ዕድል ለመፍጠር ነው የሞከርነው። አንዳንድ ጊዜ በተጫዋቾች መካከል ያለው የአዕምሮ ልዩነት ስህተት ከመስራት በስተቀር በአብዛኛው ጨዋታ ጥሩ ነው። የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። በተለይ በመጀመርያው አርባ አምስት ያገኘነውን የጎል ዕድሎች ብናገባ ኖሮ ጨዋታው የተለየ መልክ ይኖረው ነበር።
ስለኳስ ቁጥጥር ብልጫ
“ከሁለቱም አንፃር ነው። ባለፉትም ጨዋታዎች ምን አልባት የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ አልነበርንም። በአብዛኛው በኳስ ቁጥጥር ላይ የተሻለ ቡድን ሜዳ ላይ እንዳለን ቁጥሮችም ይናገራሉ። ዛሬ ግን ከሜዳው ምቹነት ከተጋጣሚያችን ፈጣን የማጥቃት ሁኔታ አንፃር ኳሱን እኛ ጋር በማቆየት እነርሱ ማጥቃት እንዳይችሉ አድርገናል። እኛም የጎል ዕድል ለመፍጠር ነበር ያሰብነው አልተሳካልንም።”