ሪፖርት | የድቻ እና የባህር ዳር ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሆኗል

በዛሬው የመጨረሻ ጨዋታ ወደ መቀመጫ ከተማቸው የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች ከወላይታ ድቻ ጋር 0-0 ተለያይተዋል።

ወላይታ ድቻ በፋሲል ከነማ ከተሸነፈበት ጨዋታ አሰላለፍ ውስጥ ለዛሬ ደጉ ደበበን በመልካሙ ቦጋለ ቦታ ተክቷል። በተመሳሳይ በጅማ አባ ጅፋር የተሸነፉት ባህር ዳሮች ባደረጓቸው 5 ለውጦች አበበከር ኑራ ፣ ሣለአምላክ ተገኘ ፣ ግርማ ዲሳሳ ፣ አደም አባስ እና በረከት ጥጋቡ በፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና አብዱልከሪም ኒኪማ ምትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታውን ከፍ ባለ የማጥቃት ጉልበት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የፍፁም ዓለሙን ንክኪዎች ተከትሎ በፈቱዲን ጀማል እና ዓሉ ሱለይማን ጥሩ የማግባት ዕድሎችን አግኝተው ነበር። ቡድኑ ሙሉ አቅሙን ወደ ወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል ላይ ባዋለባቸው ቀዳሚ 25 ደቂቃዎች የቁጥጥር ብልጫ ቢኖረውም የወላይቻ ድቻን ጥብቅ መከላከል አስከፍቶ ተደጋጋሚ ዕድሎችን አልፈጠረም። የተሻለ በነበረው ሙከራ 13ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱለይማን ከቀኝ ያሻማውን ኳስ ፍፁም ሳጥን ውስጥ በግማሽ ቮሊ ወደ ግብ ልኮት ወደ ላይ ወጥቷል።

ወላይታ ድቻዎች የመከላከሉ ሥራ ላይ ለመቆየት ቢገደዱም ቀስ በቀስ ከሜዳቸው በመውጣት በመልሶ ማጥቃት ለመግባት ያደረጉት ጥረት እምብዛም ጥራት አልነበረውም። የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ 26ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና ወደ ላይ የተነሳው አጋጣሚ ነበር። በጀመሩበት መንገድ ጫና አሳድረው መቀጠል ያልቻሉት ባህር ዳሮችም ፍፁም ከሳጥን ውጪ እንዲሁም ፈቱዲን ከመሀል ሜዳ ባደረጓቸው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠት ሞክረው አልተሳካላቸውም።

አጋማሹ ለማጥቃት ሲቃረብ ወላይታ ድቻዎች ጫናው ቀለል ብሏቸው ታይተዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ እንድሪስ ሰዒድ ወደ ግራ ካደላ ቅጣት ምት ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በኋላ በጭማሪ ደቂቃ የሚፈልጉትን የመልሶ ማጥቃት ቅፅበት አግኝተውም ነበር። በዚህም ቀልኪዳን ዘላለም ከተከላካዮች ጀርባ በመግባት ከግራ እያጠበበ ረዘም ያለ ርቀት ኳስ እየነዳ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ለያሬድ ዳዊት ለማሳለፍ የመሞከረው ኳስ በቀላሉ ጎል ሊሆን የሚችል የነበረ ቢሆንም መናፍ ዐወል ስለጨረፈው የያሬድ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስም የጣና ሞገዶቹ በጥሩ ንክኪዎች ወደ ሳጥን እየደረሱ ጫና በመፍጠር ጀምረዋል። የጦና ንቦቹ ግን ከመጀመሪው አጋማሽ አጀማመር በተለየ በጥልቅ ከመከላከል ይልቅ መልሶ ማጥቃትን የቀላቀለ ምላሽ መስጠትን መርጠዋል። ሆኖም 65ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱለይማን ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በፅዮን መርዕድ ጀርባ ከፍ አድርጎ ልኳት ወደ ውጪ ከወጣችው ኳስ በቀር ጥድፊያ የተሞላበት የባህር ዳር ቅብብልም ሆነ የወላይታ ድቻ በደካማ የመጨረሻ ቅብብሎች የታጀበ መልሶ ማጥቃት ንፁህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ተስኗቸዋል።

በመጨረሻው 15 ደቂቃ ጨዋታው የተሻለ ሲነቃቃ ባህር ዳሮች ከሳጥን ውጪ መሞከርን እንደ አማራጭ ወስደዋል። በዚህም 77ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ከረጅም ርቀት ያደረገው ድንቅ ሙከራ በግቡ ቋሚ ሲመለስ 82ኛው ላይ ደግሞ ተመስገን ደረሰ ያደረገው ተመሳሳይ ሙከራ በፅዮን መርዕድ ጥረት ድኗል። በቀሩት ደቂቃዎችም ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ጭምር ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩት ባህር ዳሮች የወላይታ ድቻን ጠንካራ መከላከል መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል። 

ቡድኑ በጭማሪ ደቂቃ በተመስገን ደረሰ የመቀስ ምት እና በፍፁም ዓለሙ የቅጣት ምት ያደረጋቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ፅዮንን ማለፍ ሳይችሉ ጨዋታው ያለግብ ተቋጭቷል።

በውጤቱ ወላይታ ድቻ በ35 ነጥቦች ወደ 3ኛ ደረጃ ሲሻገር ባህር ዳሮች ነጥባቸውን 26 አድርሰው በግብ ልዩነት ሁለት ደረጃ በማሻሻል 10ኛ ሆነዋል።

ያጋሩ