የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-0 ባህር ዳር ከተማ

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ – ባህርዳር ከተማ

ወደ ውጤት ያለመቀየር ጫና

“መግቢያ ላይ እንደተናገርኩት ደጋፊውን ለማስደሰት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከነበሩ ጉጉቶች የተነሳ ብዙ ኳሶችን አምክነናል፡፡ ግን በጠቅላላ ጨዋታው በመጀመሪያውም በሁለተኛውም አርባ አምስት በኳስ ቁጥጥሩም ፣ ግቦችንም በመሞከር ፣ አጥቅቶ በመጫወት ፣ እኛ የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁንም ግን አንድ ሦስተኛ የማጥቂያ ክፍል እነርሱ ጋር ስንደርስ ግብ ለማግባት ከመቸኮል የተነሳ የምናመክናቸው ኳሶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ለቀጣይ ጨዋታ ብዬ ነው የማስበው፡፡

ስለተደረጉ የተጫዋች ቅያሬዎች

“የግርማ ድንገት መውጣት የምፈልገውን ነገር አላሳካውም ፤ በጉዳት ምክንያት መውጣቱ፡፡ የታክቲክ ለውጥ ነው ያደረግነው፡፡ ተመስገንን ወደ ፊት አድርገን በዳይመንድ እንዲጫወቱ እና በማጥቃት ኃይላችን ዓሊን የሚያግዝ ሰው መጨመር ነበር፡፡ ግን የግርማ መጎዳት እንደገና አንድ ሰው እንድንቀንስ አድርጎናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ እንዳየኸው ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን አግኝተን ወደ ጎል መቀየር ባለመቻላችን ብቻ ነጥብ ተጋርተን ልንወጣ ችለናል፡፡”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው

“የፕሪምየር ሊጉ ውድድር እየተጠናቀቀ መሆኑን እና የባህርዳር ቀጣይ ተጋጣሚ ፋሲል መሆኑን እናውቃለን እና ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ነው የተጫወትነው፡፡ ምክንያቱም ፈጣን አጥቂዎች አሏቸው ፣ ሚድፊልዶቻቸውም ጥሩዎች ናቸው፡፡ ከምንም የበለጠ ደጋፊዎቻቸው አሉ እና ቀላል እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ በጣም ተጭነው እንደሚጫወቱ እናውቃለን፡፡ ሜዳ ላይ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነበርን፡፡ አንድ ለአንድ ከበረኛችን ጋር እንዲገናኙ አልፈቀድንም፡፡ በመስመር በኩልም ክፍተት አልሰጠንም፡፡ ከሜዳውም ጋር እየተላመድን ስለነበር በዛ ላይ ከሽንፈት ስለመጣን በጣም በጥንቃቄ ተጫውተን አስፈላጊ ነጥብን አግኝተናል፡፡

በርካታ ደቂቃን ስለመከላከላቸው

“እኛ በሎው ብሎክ ነው የተከላከልነው፡፡ አስፈላጊ የሆነ የመከላከል አደረጃጀት ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዙር እነሱ በተናጥል እያገኙን ፣ ብዙ ድሪብል እያደረጉ አሸንፈውናል፡፡ ከዛ ስህተቶቻችን ለመማር ያየናቸው ቪዲዮዎች አሉ፡፡ እነሱ ተጫዋች ቀንሶ የመምጣት አቅም አላቸው እነ ፍፁም ቀላል ተጫዋቾች አይደሉም፡፡ እንደዚህም ሆኖ ዕረፍት ልንወጣ ስንል በመልሶ ማጥቃት ያገኘናቸው ወርቃማ ዕድሎች ነበሩ ፤ አልተጠቀምንበትም፡፡ በእኔ በኩል ጥሩ ነጥብ ነው ብዬ የማስበው፡፡”

ያጋሩ