ሪፖርት | ዐፄዎቹ ተጠባቂውን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው የረፋዱ ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ራሱን አቆይቷል።

ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ በተከላካይ መስመር ላይ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ያኩቡ መሀመድ እና መሀሪ መና ወጥተው በምትካቸው ተስፋዬ በቀለ እና ሰለሞን ሃብቴ ሲገቡ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን ከረታው ስብስብ ላይ በተመሳሳይ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ከድር ኩሊባሊ እና ይሁን እንደሻው ወጥተው በምትካቸው ሀብታሙ ተከስተ እና ሽመክት ጉግሳ ወደ አሰላለፍ መጥተዋል።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞው የፋሲል ከነማ ቦርድ አመራር ለነበሩት አቶ መለሰ ከበደ የአንድ ደቂቃ ህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባልን የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን ነበር።

ቀዳሚው አጋማሽ ምንም እንኳን እምብዛም ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች የተመለከተንበት አጋማሽ ባይሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ታይቶበታል። ፋሲል ከነማዎች የተሻለ ኳስ ቁጥጥር ድርሻን ይዘው በተወሰነ መልኩ ወደ ግራ ባደላ መልኩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሙከራ ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ፈጠን ባሉ መልሶ ማጥቃቶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።

እንደ ፈጣን አጀማመራቸው በአጋማሹ ምንም ዓይነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ፋሲል ከነማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ቀስ በቀስ ግን በጨዋታው ተፅዕኗቸው እየቀነሰ መጥቷል። በሂደት ወደ ጨዋታው የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ግን ቀስ በቀስ ወደ ፋሲል ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ ችለዋል። በ24ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ፍሬው ሰለሞን ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ በመያዝ አፈትልኮ ቢገባም ያገኘውን ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚ አምክኗል። ጨዋታው ከውሃ ዕረፍት ሲመለስ በተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በ34ኛው እና 36ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ከመስመር ከተሻሙ ኳሶች ሁለት አደገኛ አጋጣሚዎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

በ38ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጉዳት ያስተናገደው አስቻለው ታመነ ሜዳ ላይ መቀጠል ባለመቻሉ በአምሳሉ ጥላሁን ተቀይሮ ከሜዳ በመውጣቱ ፋሲሎች የመስመር ተከላካዩ ሰዒድ ሁሴንን በመሀል ተከላካይነት ለመጠቀም ተገደዋል። በ39ኛው ደቂቃም እንዲሁ በሲዳማ በኩል በተፈጠረ ዕድል ዳዊት ተፈራ ከመሀል ሜዳ ተጫዋቾችን አልፎ በመጠጋት ከሳጥን ውጪ ያደረጋት እና ሳማኪ ያዳነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራ ነበረች።

ተጋግሎ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመሪያው ሁሉ ፈጠን ያሉ ከሳጥን ሳጥን የሚደርሱ የማጥቃት ሂደቶች የነበሩ ቢሆንም ግብ ጠባቂዎችን የፈተኑ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን እንደ መጀመሪያው ሁሉ ውስንነት የነበረበት አጋማሽ ነበር። ክፍት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ የሲዳማ ቡና የማጥቃት ማዕከል የነበረው ይገዙ ቦጋለ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲያደርግ የተመለከትን ሲሆን ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርጉ የነበሩት ፋሲሎች ደግሞ ኳሶችን ወደ ሳጥን ማድረስ ቢችሉም ንቁ የነበረው ተክለማርያም ሻንቆ የሚቀመስ አልሆነም።

ቀስ በቀስ እያየለ የመጣውን የፋሲል ከነማዎችን ጫና ለመቋቋም ሲዳማ ቡናዎች ከሳልሀዲን ሰዒድ ውጪ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ራሳቸው ሜዳ በመሳብ በጥልቀት በመከላከል ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም በአጋማሹ በተሻለ ፍላጎት ለማጥቃት ሲጥሩ የነበሩት ፋሲሎች ግን ይበልጥ ጫና ከመፍጠር አልቦዘኑም።

በ65ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ጠርዝ ያቀበለውን ኳስ በዛብህ መለዮ ተቆጣጥሮ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ሲልከው ተክለማርያም ሻንቆ ባዳነበት ኳስ ማስጨነቃቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በ75ኛው ደቂቃ ላይ ግን መሪ መሆን ችለዋል። በረከት ደስታ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሻማው ኳስ በሲዳማ ተከላካዮች ሲጨራረፍ አግኝቶ ከደቂቃዎች በፊት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓልነበር።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች አዎንታዊ ምላሽ ያሳያሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሚፈለገው ልክ ወደ ፊት እየደረሱ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልተመለከትንም። በአንፃሩ በተሻለ መልኩ ኳሱን በመያዝ ጨዋታውን የመቆጣጠር ፍላጎት የነበራቸው ፋሲሎች በአንዳንድ አጋጣሚዎችም አደጋ ለመመፍጠር ጥረት በማድረግ ጨዋታውን 1-0 በማሸነፍ ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 40 በማሳደግ ከመሪው ያላቸውን የ10 ነጥብ ልዩነት ሲያስቀጥሉ ሲዳማዎች ደግሞ በ34 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።

ያጋሩ