የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-1 ፋሲል ከነማ

በረፋዱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ወሰኝ ሦስት ነጥብ ካሳካ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ በኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለወሳኙ ነጥብ

“ ከመሪው ብቻ ሳይሆን ከሚከተለን ሲዳማ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ነበር። ሜዳው በሚፈቅደው ከጨዋታ ጋር ምንም በፍጥነት ጎል ባናስቆጥርም ከጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፈን ልንወጣ ችለናል።

ስለቡድኑ መሻሻል

“ዛሬ የተሻሻልነው የኳስ ቁጥጥር ላይ ነው። በትዕግስት መጫወት ላይ ነው። ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተገኝቶ ጎል ማስቆጠሩን ደግሞ በቀጣይ አሻሽለን እንመጣለን።

ስለበዛብህ ቅያሪ

“ ይሁን ሲገባ በሁለት የተከላካይ አማካኝ ለመጫወት ነው። ምክንያቱም እየመራህ ነው ፤ ሰዓት አልቋል። በዛ ላይ በዛብህ ደክማለች ወደ አጥቂው እየሄደ ፣ ወደ ኋላም እየተመለሰ በማገዙ ብዙ ድካም ነበር። እርሱን አሳርፈን ሌላ ኃይል መጠቀም ስለነበረብን ነው።

ስለዋንጫ ፉክክሩ

“እንግዲህ እርሱን ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ከፊት የምታገኘውን ተጋጣሚ እያሸነፍክ ከሄድክ ከዛ በኋላ የሚመጣውን መቀበል ነው።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“ ይዘነው የገባነው ታክቲክ በተወሰነ መልኩ ተግባራዊ ሆኗል። የምንነጥቃቸውን ኳሶች በሂደት ቀስ እያልን እያጠቃን ተጋጣሚ ላይ አንድ ነገር መፍጠር ነበር ፤ እርሱ ተሳክቶልናል። ግን የፈጠርናቸውን ያህል ማግባት አልቻልንም። ብዙ ዕድሎችን አግኝተን አለመጠቀማችን ዋጋ አስቀፍሎናል። ያው ልጆቹ በጣም ውጪ ሆነዋል ባልጠበቁት ሁኔታ ጎል ስለተቆጠረብን።

በጨዋታው ስለወሰዱት የበላይነት

“የጨዋታ የበላይነት እነርሱም እኛም ወስደናል ለማለት አይቻልም። ዋናው ነገር ታክቲካሊ ዲሲፒሊን ሆኖ መጫወት ነው። የነበረን ነገር ጥሩ ነበር ፤ ጎሉ እስከተቆጠረብን ድረስ። ነገር ግን የእግርኳስ ተፈጥሮ እንደዚህ ነው። አንዳንዴ ባልጠበክበት ሁኔታ ጎል ይገባብሀል።

ያገኙትን የጎል አጋጣሚ ስለአለመጠቀም

“ የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው። አንደኛው በተለይ ይገዙ በጣም መረጋጋት አይታይበትም ነበር። ዛሬ በብዙ ነገሩ ጥሩ አልነበረም። በጣም ጉጉት ነበረው። ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ፉክክር ውስጥ መሆኑ ትንሽ እንዳይረጋጋ ያደረገው ይመስለኛል።