ሪፖርት | የጨዋታ ሳምንቱ በአቻ ውጤት ተደምድሟል

የጫላ ተሺታ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ወልቂጤ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ እንዲጋራ አድርጋለች።

ወልቂጤ ከተማ አርባምንጭን 3-0 ከረታበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙን በሮበርት ኦዶንካራ ምትክ ሲያስገባ ዮናታን ፍሰሀ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ጫላ ተሺታ እና አቡበከር ሳኒም በተስፋዬ ነጋሽ ፣ ዮናስ በርታ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና አበባው ቡታቆ ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል። ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ የተጋራው አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ ዘሪሁን አንሼቦን በቴዎድሮስ ሀሙ እንዲሁም ፍፁም ጥላሁንን በእንዳለ ከበደ በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ቀዳሚው አጋማሽ በፍጥነት ዝግ ያለ እና ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትን ሙከራ ያልተመለከትንበት ሆኖ አልፏል። ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ከሚሞክሩት ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ የተሻለ ጫና አሳድሮ ወልቂጤ ሜዳ ላይ የመጀመሪያ ደቂቃዎችን ቢያሳልፍም 3ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ ከዳኞች ዕይታ ውጪ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ውስጥ በቀኝ ነፃ ሆኖ የገባበት እና ወደ ግብ የላከው ኳስ በዮናትን ፍሰሀ የመከነበትን ዕድል ብቻ አስመልክቶናል። ቡድኑ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ የተሳሳቱ ቅብብሎች በሂደት ከሙከራም ከኳስ ቁጥጥር ብልጫም ውጪ አድርገውታል።

በቀሪው የአጋማሹ ጊዜ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ማሳካት የቻለት ወልቂጤዎች በቀኝ በጫላ ተሺታ በኩል ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ጌታነህ ከበድ በሳጥኑ ዙሪያ ያደረጋቸውን የርቀት ሙከራዎች ብቻ አስመዝግበዋል።

ሰራተኞቹ ኳስ በመያዙ የተሻሉ ይሁኑ እንጂ መሀል ላይ በሚታዩ መነጣጠቆች የቀጠለው ጨዋታ 25ኛው ደቂቃ ላይ ኤሊያስ አህመድ ሳጥን ውስጥ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ያበረደለትን ኳስ ሲመታ ዉሀብ አዳምስ የተደረበበት አጋጣሚ ብቻ የተሻለ ዓይን ሳቢ ቅፅበት ነበር። ከዚህ በኋላ ይበልጥ የተዳከመ እንቅስቃሴ የታየበት አጋማሹ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ጥሩ የግብ ዕድል ተፈጥሮበታል። በዚህም ሙሉቀን በተከላካዮች መሀል የሰነጠቀው ኳስ ለፍፁም ጥላሁን ጥሩ ዕድል ቢፈጥርም በተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው መሀል አልፎ ለማስቆጠር የጣረው ፍፁም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ጫና መፍጠር የጀመሩት አዲስ አበባዎች ጎል አግኝተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ሙለቀን አዲሱ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ውሀብ አዳምስ በግንባሩ ለማውጣት ባደረገው ሙከራ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። 

ወልቂጤዎች ከግቡ በኋላ አሁንም ኳስ ተቆጣጥረው ዕድሎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ሆኖም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሪችሞንድ ኦዶንጎን ያማከሉ ረጅም ኳሶችን ወደ ፊት ይጥሉ የነበሩት አዲስ አበባዎች በንፅፅር የተሻለ አስፈሪነት ነበራቸው።

ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ የወልቂጤዎች ጫና ከፍ ያለ ቢመስልም ቡድኑ የግብ ዕድል ፈጥሮ የታየው 75ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከግራ በረጅሙ ወደ ሳጥን የጣለውን ኳስ ጫላ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ወደ ላይ ሲወጣበት ነበር።

አዲስ አበባዎችም የመልሶ ማጥቃት ፍላጎታቸው እየቀነሰ ወደ ጥንቃቄው እያመዘኑ ሄደዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ እስከፍፃሜው የዘለቀው ጨዋታ በመጨረሻ ተነቃቅቷል። የአቻነቱን ጎል ለማግኘት ደካማ ምላሽ የሰጡት ወልቂጤዎች ባለቀ ሰዓት ከቆመ ኳስ ጎል አግኝተዋል። በዚህም 89ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ያሻማውን የማዕዘን ምት ጫላ ተሺታ በግንባሩ በመግጨት ግብ አድርጎታል። 

በጭማሪዎቹ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ወደ ሳጥን የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ቢታዩም ጨዋታው ሌላ ግብ ሳያስተናግድ 1-1 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ በ29 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዲስ አበባ ከተማ በ22 ነጥቦች በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል።

ያጋሩ