የባህር ዳር ስታዲየም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል

ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ኢትዮጵያ በሜዳዋ ለማድረግ የባህር ዳር ስታዲየምን በካፍ ብታስገመግምም ውድቅ ሆኖባታል፡፡

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ መደረግ ይጀምራል፡፡ በምድብ 4 – ከማላዊ ፣ ግብፅ እና ጊኒ ጋር የተደለደለችሁ ኢትዮጵያ በሜዳዋ ያለባትን ጨዋታ ለማከናወን የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ከቀናቶች በፊት በካፍ ባለሙያው ሚስተር ኢቫን ኪንቱ አማካኝነት ሁሉንም የሜዳውን ክፍል ፣ የመጫወቻ ሳሩን ፣ የመልበሻ ክፍሎቹን እና አጠቃላይ የስታዲየሙን ይዘት በባለሙያው አማካኝነት ያስገመገመች ቢሆንም በውጤቱ ካፍ ስታዲየሙን ሳያፀድቀው ቀርቷል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገፁ እንዳስነበበው ከካፍ በተላከለት ደብዳቤ መሰረት የስታዲየሙ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሶ መስራት እንደሚገባ በመግለፅ በ10 የተለያዩ መመዘኛዎች ላይ ነጥቦች ተቀምጦለታል። ካፍ የመጫወቻ ሜዳን ጨምሮ የውስጥ ክፍሎችን እና አጠቃላይ የስታዲየሙን ቅጥር ግቢ የተመለከቱ በርካታ ነጥቦችን ያሰቀመጠ ሲሆን ጥቂቶችን ለመጥቀስ :-

የመጫወቻ ሜዳው በአዲስ የተፈጥሮ ሳር እንዲተካ ፣ አውቆማቲክ የውሃ ማጠጫ እንዲኖረው እና በዘርፉ በሚሰራ ኩባንያ አማካኝነት የመግጠም እና እንክብካቤ ስራ እንዲሰራ ፣ የተጠባባቂ እና የጨዋታ አመራሮች መቀመጫ የኢንተርናሽናሽናል ስታንዳርድ እንዲያሟላ ፣ ስታዲየሙ ፓውዛ እንዲገጠም እና ተለዋጭ የኃይል አቅርቦት እንዲኖረው ፣ የመልበሻ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መልክ እንዲሰሩ ፣ ካፍ የሚጠቀምባቸው ቢሮዎች እና የኳስ አቀባዮች እና ባንዲራ የሚይዙ ታዳጊዎች ክፍል እንዲሟላ ፣ ከ23 በላይ የሆኑ የሜዲካል ቁሳቁሶች እንዲሁም የሜዲካል ክፍሎች እንዲሟሉ ፣ የተመልካች ሙሉ የስታዲየም ክፍሎች እንዲታደሱ እና ለአንድ ሰው አንድ ደረጃውን የጠበቀ መቀመጫ ወንበር እንዲኖር ፣ መቀመጫዎችን የሚሸፍን ጣርያ ከግምት ውስጥ እንዲገባ ፣ የምግብ እና መዝናኛ አገልግሎት በሁሉም የስታዲየም ክፍል እንዲኖር ፣ ስታዲየሙ የደህንነት እና የእሳት አደጋ ሰርቲፍኬት ከሚመለከተው አካል እንዲያገኝ እና የሚዲያ ትሪቡን በተሟሉ ቁሳቁሶች እንዲደራጅ የሚሉት ይገኙበታል።

በጥቅምት ወር የካፍ የስታዲየሞች መስፈርትን ባለማሟላቱ ዕገዳ ተጥሎበት የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም ለሁለተኛ ጊዜ የካፍ የቅጣት በትር አርፎበታል፡፡ ቀደም ባለው ዕገዳ የተነሳ ከሜዳዋ ውጪ ደቡብ አፍሪካ ላይ የማጣሪያ ጨዋታዋን ከዚህ ቀደም አድርጋ የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ20 ቀናት በኋላ ከማላዊ ጋር ከሜዳዋ ውጪ ከተጫወተች በኋላ በባህር ዳር ላይ ግብፅን ትገጥማለች የሚል ትልቅ ተስፋ የነበረ ቢሆንም ሜዳው ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታዋን ማድረጓ ዕርግጥ የሆነ ሆኗል፡፡