ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

ሦስተኛው የዓበይት ጉዳይ ፅሁፋችን አሰልጣኞች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች የተነሱበት ነው።

👉 “ግብ ካገባን በኋላ ውጤቱን ለማስጠበቅ ልጆቻችን የመሸሽ ነገር ይታይባቸዋል”

ከሰሞኑ በሚኖሩ የድህረ ጨዋታ አስተያየቶች በተደጋጋሚ እያደመጥናቸው ከምንገኙ ሀሳቦች መካከል “ግብ ካገባን በኋላ ውጤቱን ለማስጠበቅ ልጆቻችን የመሸሽ ነገር ይታይባቸዋል” የሚል ሀሳብ ይገኛል።

በተለይ እንደ እኛ ሀገር ከጨዋታ መንገድ ይልቅ ውጤት አብዝቶ በሚፈለግበት እግርኳስ ውስጥ በሁለተኛ ዙር ውድድሮች ላይ ጥንቃቄን የቀላቀሉ አጨዋወቶች እና የተገኘችን ነገር የማስጠበቅ ሂደት የሁሉም የጋራ (Default) ስልት እስኪመስል ድረስ የቡድኖች የጋራ መገለጫ ሆኖ ተመልክተናል። በዚህ ሂደት በተለይ ‘ለማስጠበቅ የተመቸ ውጤት’ ሲኖር ቡድኖች የመከላከል ሂደትን መከተላቸው የተለመደ ነው። ነገር ግን ይህ እንደ ቡድን የሚደረግን ወደ ኋላ የማፈግፈግን ሂደት በተጫዋቾቹ ውስጥ ከሚፈጠር የስጋት እሳቤ ብቻ የሚመነጭ ነው ብሎ መውሰድ ትንሽ አስቸጋሪ ነው።

አብዛኞቹ አሰልጣኞች ይህን ወደ ኋላ የመሰብሰብን ሂደት ከሜዳ ጠርዝ የማጥቃትን ሀሳብ በማስተጋባት እንዲሁም በአውንታዊ ቅያሬዎች እና በጨዋታ ዕቅድ ክለሳ ለማረም ከመሞከር ይልቅ ከአዎንታዊነት በተቃራኒ የቆሙ ቅያሬዎች እና ሌሎች ሂደቶች እየፈጠሩ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተጫዋቾችን በተናጠል ተወቃሽ ማድረጉ ከተጠያቂነት ለመዳን ከሚደረግ ጥረት ለይቶ መመልከት ከባድ ነው።

በተመሳሳይ ቡድኑ ሆኖለት ውጤቱን አስጠብቆ መውጣት ሲችል ደግሞ የተከተለው አጨዋወት የታሰበበት እና ታቅዶ የተደረገ እንደሆነ የሚጠቁሙ አስተያየቶችን ከአሰልጣኞች መስማታችን የነገሩን ኃላፊነት በውጤቱ ላይ ተመስርቶ የመውሰድ አዝማሚያ እንዳለ የሚጠቁም ነው።

👉 የተመስገን ዳና አስተያየት

“በራሳችን የእኛ ቡድን ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን የእኛ ተጋጣሚ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም አሉታዊ እግር ኳስን ነበር ስመለከት የነበረው፡፡ ይሄ ዓለም የሚመለከተው እግር ኳስ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ኳስ መጫወት ከባድ ነው፡፡”

ይህን ያለው ቡድኑ በጨዋታው 54% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበረው እና በጨዋታው በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ሁለት ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ያደረገው ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ነው።

ዓለም ላይ ይህ ነው የሚባል የእግርኳስ የውጤታማነት መንገድ በሌለበት እግርኳስን ከመዝናኛ አንፃር ብቻ በመመልከት ለዕይታ መስህብ ያለው እግርኳስ የተጫወቱ ቡድኖችን የማፅደቅ በተቃራኒው ደግሞ አሉታዊ እግርኳስን ደግሞ የማውገዝ ዝንባሌ በስፋት ይታያል። እግርኳስ ከመዝናኛ ባለፈ የፉክክር ስፖርት እንደመሆኑ ይህ ‘ፉክክር’ የሚለው እሳቤ ደግሞ አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመውሰድ ይበጀኛል ያለውን መንገድ እንዲከተል ያስገድዳል። በመሆኑም የጨዋታ መንገድ (Style) የሚለው ምርጫም ከዚህ የሚመነጭ ይሆናል።

ስለዚህም አሰልጣኞች የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ ከመተቸት ባለፈ ራሳቸው በያዙበት መንገድ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ውጤት ሊቀይሩባቸው ስለሚችሉባቸው መንገዶች አድምተው በመስራት ቡድናቸው ተጋጣሚ የሚደቅንበትን ፈተና በሙሉ መወጣት በሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረግ እንጂ ‘ሌሎች በእኛ መንገድ አልተጫወቱምና…’ በሚል የነቀፌታ እሳቤ መመዘን ውሃ የሚያነሳ አይደለም።

👉 ጉዳት ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ

በእግርኳስ ውስጥ ስለሚከሰቱ ጉዳቶች ስናስብ ምናልባት በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጡት ተጫዋቾች ናቸው። ሆኖም በሊጉ ባልተለመደ መልኩ አንድ አሰልጣኝ በጉዳት ላይ ይገኛሉ።

የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድናቸው ከመከላከያ ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ወቅት ከተቀመጡበት ሲነሱ ጉልበታቸው ላይ የህመም ስሜት የተሰማቸው መሆኑን ተከትሎ ወደ ህክምና ተቋም አምርተው ባደረጉት ምርመራ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸዋል። በዚህም መነሻነት አሰልጣኙ ከባለፈው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ እንደቀደመው ተነስተው ቡድኑናቸውን እየመሩ አይገኙም። ያም ቢሆን በዚህ ህመም ውስጥ ሆነው ቡድናቸውን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከህመም ጋር እየታገሉ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በቀጣይም ቀዶ ጥገናው የሚያደረግ ከሆነ ለተወሰኑ ጊዜያት ከሜዳ የሚያርቃቸው መሆኑ ቢታመንም በህመም ውስጥ ሆነው ምን ያህል ቡድኑን በሜዳ ተገኝተው ይመራሉ የሚለው ጉዳይ በቀጣይነት ይጠበቃል።

👉 ጳውሎስ ጌታቸው ተመልሰዋል

ከወልቂጤ ከተማ ጋር ከወራት በፊት ከተለያዩ ወዲህ ለጥቂት ጊዜያት ከዕይታ ርቀው የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ዳግም ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጋር የተለያዩት አዲስ አበባ ከተማዎች በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ህልም እውን እንዲያደርጉ በማሰብ በሊጉ ልምድ ያላቸውን አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን መሾማቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳን የወረቀት ሥራዎች ባለማለቃቸው በሜዳ ውስጥ ተገኝተው ቡድናቸውን መምራት ባይችሉም አሰልጣኙ እና ምክትላቸው እዮብ ማለ በተመልካቾች መቀመጫ ላይ ሆነው የዚህን ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ተከታትለዋል።
አዲሱ ቡድናቸው በመጀመሪያ ጨዋታ ከቀድሞ ቀጣሪዎቻቸው ላይ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግን ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

አዲሱ የአሰልጣኞች ቡድን የዋና ከተማዋን ቡድን የመታደግ አቅሙ እስከምን እንደሆነ በቀጣይ ጨዋታዎች ይጠበቃል።