የመጨረሻው ፅሁፋችን ሌሎች ትኩረት የሳቡ የሳምንቱ ጉዳዮች ቀርበውበታል።
👉 የባህር ዳር ውድድር ጅማሮውን አድርጓል
ከ22ኛ ሳምንት አንስቶ እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ድረስ ውድድሩን የማስተናገድ ኃላፊነቱን የተረከበችው ባህር ዳር ከተማ እንግዶቿን ተቀብላ የመጀመሪያውን የጨዋታ ሳምንት በስኬት አስተናግዳለች።
በሊጉ በተለይ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በመጫወቻ ሜዳ ረገድ የሚታዩ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን። ከዚህ አንፃር ግን የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ በሀገራችን የመጫወቻ ሜዳዎች ጥራት ታሪክ ምርጡ እንደሆነ ማስተዋል ችለናል።
ፍፁም ለዕይታም ሆነ ኳስን ለማንሸራሸር የተመቸው ሜዳው ከሌሎች ስታዲየሞች በተለየ በጨዋታዎች የአጋማሽ የዕረፍት ጊዜ በሀገራችን እምብዛም ባልተለመደ መልኩ የሜዳውን ሁኔታ የሚከታተሉ የተለያዩ ባለሙያዎች እንክብካቤ ሲያደርጉለት ተመልክተናል።
ሌላኛው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ከመጀመሪያው የጨዋታ ዕለት መጠናቀቅ በኋላ ተጫዋቾች የማማሟቋያ ሥራዎችን በሚሰሩባቸው የሜዳ ክፍሎች ላይ ሳሩ ከጫና መብዛት የተነሳ በተወሰነ መልኩ የቀለም መለወጥ አዝማሚያ ማሳየቱን ተከትሎ የሊጉ አስተዳዳሪ አካል ወክለው የተገኙት የቦርድ ሰብሳቢው እና ሥራ አስኪያጁ ከክለቦች ጋር በመነጋጋር ከኳስ ውጪ በጥቂት የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰሩ የማፍታቻ ሥራዎች ከዋናው ሜዳ ውጪ ተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ ጀርባ ላይ እንዲሰሩ ያደረጉትም ጥረት የሚመሰገን ተግባር ነው።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ውድድሩ ሲደረግበት የነበረው የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ በመጠን አነስ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርከት ያሉ ቡድኖች በመጠን በጣም ሰፊ ከሆነው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል ተቸግረው ተመልክተናል።
ከዚህ ባለፈ ይህ ክትትል ሜዳው በቀን ሦስት ጨዋታዎችን እያስተናገደ በቀጣዮቹ ቀናት ከሚኖርበት ጫና አንፃር የሚፈጠረውን ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ሁለት ተጨማሪ ዳኞች በጨዋታዎች
በባህር ዳር ከተማ ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ እስከ ውድድር ዘመኑ መገባደጃ በሚኖረው የሊጉ ቆይታ አዳዲስ ነገሮችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ከእነዚህ ውስጥ ከውድድሩ መጀመር አንድ ቀን አስቀድሞ እንደተበሰረው በውድድሩ ላይ የሚኖሩ የዳኝነት ውሳኔ መዛነፎችን ለመቀነስ በማለም በሊጉ ሁለት ተጨማሪ ዳኞች ከሁለቱ ግቦች በስተጀርባ እንዲሰየሙ መደረጉ አንዱ ነው። ከዳኝነት ጋር በተያያዘ በርካታ ወቀሳዎች እየቀረቡበት በሚገኘው የሊጉ ውድድር በአንፃራዊነት የተሻለ ፍትህን ለማስፈን የሚረዱትን የቴክኖሎጂ አማራጮች ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ እስክንመጣ መሰል አሰራሮች መተግበር መጀመራቸው በመልካምነቱ የሚነሳ ጉዳይ ነው።
ከዚህ ሂደት ጋር በተያያዘ በአክሲዮን ማህበሩ ለተጨማሪ ዳኞች የሚሆን በጀት የለኝም ማለቱን ተከትሎ በአክሲዮን ማህበሩ እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መካከል መጠነኛ ውዝግቦች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም ፌደሬሽኑ በአቋሙ በመፅናቱ እና በኋላ ላይ በተደረጉ ገንቢ ውይይቶች ይህ ሀሳብ ገቢራዊ ሊሆን በቅቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መሰል እርምጃዎችን በመውሰድ የውድድሩን መንፈስ ከቅሬታዎች የፀዳ ለማድረግ እየተረጉ የሚገኙ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው።
👉 ቤተኛው ውሻ
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ የሊጉ ውድድር ሲጀመር አንድ የተለየ እንግዳ ክስተትን ተመልክተናል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከመከላከያ ባደረጉት የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ወቅት በ50ኛው ደቂቃ አካባቢ ድንገት አንድ ውሻ ሀገር ሰላም ብሎ ወደ መጫወቻ ሜዳ ውስጥ ይገባል። ሜዳውን አቋርጦ የመሄድ ፍላጎት የነበረው ውሻው በመጀመሪያ ዙር በጨዋታው አልቢትር ዮናስ ካሳሁን አስገዳጅነት ከሜዳ እንዲወጣ የተገደደ ሲሆን በዚህ ያለበቃው ውሻው ዳግም ወደ ሜዳው ተመልሷል። በዚህኛው አጋጣሚ ደግሞ በሀዲያው ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ እና ሌሎች አስገዳጅነት ሜዳውን አቋርጦ እንዲሄድ ተደርጓል።
ከአንድ ደቂቃ ለሚልቅ ጊዜ የጨዋታውን ሂደት ማስተጓጓል የቻለው ይህ ውሻ ለስታዲየሙ ቤተኛ ስለመሆኑ በሚያሳብቅ መልኩ በሌሎች ጨዋታዎችም እንዲሆ በሜዳው ሲዘዋወር አስተውለናል።
በቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን ያገኘው ይህ አጋጣሚ ምናልባት በዘንድሮው የውድድር ዘመን ፈገግታን ካጫሩ አጋጣሚዎች አንዱ ሆኖ አልፏል።
👉 ኢትዮጵያ ቡና በነጭ መለያ
ኢትዮጵያ ቡናን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቢጫ እና ጥቁር እንዲሁም ቡናማ ቀለም ካላቸው የተለያዩ መለያዎች ውጪ የተለየ ቀለም ባለው መለያ እምብዛም አላስተዋለነውም።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ገጥሞ በረታበት ጨዋታ ባልተለመደ መልኩ በነጭ መለያ ጨዋታውን ሲያደርግ ተመልክተናል። በቅርቡ አጋሩ ከሆነው “ሀ እስከ ፐ” ጋር የመለያ አቅርቦት ስምምነት የፈፀመው ቡና ከተለመዱት ቀለሞች ውጪ ሦስተኛ ነጭ መለያን ጥቅም ላይ እንደሚያውል ተገልፆ የነበረ ሲሆን በዚህም ይህ መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጥቅም ላይ ውሏል።
በሰለጠነው ዓለም ቡድኖች በየዓመቱ የሚጠቀሙባቸው ቢያንስ ሦስት የቀለም አማራጭ ያላቸው መለያዎችን ጥቅም ላይ የማዋል ልምምድ ያላቸው ሲሆን በሀገራችን ይህ ሂደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ክለቦች ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።