ቅድመ ዳሰሳ | የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ዳሰሳ

የ23ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ነገ ሲጀምሩ ከረፋድ እስከ አመሻሽ የሚደረጉትን ሦስት ፍልሚያዎች እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የመውረድ ስጋት ከፊቱ የተደቀነበት ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ የወጣበትን ሁነት ከፈጠረ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ተረቷል። በጨዋታው ቡድኑ ቀድሞ ግብ ቢያስቆጥርም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ለማስጠበቅ የሄደበት መንገድ ከአዎንታዊ አሉታዊ ጎኖቹ ያመዝኑ ነበር። ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ውጪ ለመንቀሳቀስ የፈለገው ስብስቡም የኢትዮጵያ ቡናን ጥቃቶች በሚገባ መመከት ሳይችል ቀርቷል። በዋናነት ደግሞ ካለበት ደረጃ ለመውጣት መጠነኛ ጫና ውስጥ ያለ የሚመስለው ቡድኑ ተረጋግቶ ክፍት ቦታዎችን እና አደገኛ ተጫዋቾችን የመቆጣጠር ክፍተት ታይቶበት ከሜዳ ወጥቷል። የነገ ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕናም በተመሳሳይ ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ተጋጣሚን ለማስከፈት የሚጥር በመሆኑ በቡናው ጨዋታ የታዩት የቦታ እና የሰው አያያዝ ክፍተቶች መደገም የለባቸውም። የሆነው ሆኖ በቡድኑ አሁናዊ ብቃት ደምቆ እየታየ የሚገኘው ሔኖክ አየለ ነገም ለሀዲያ ተከላካዮች ፈተና እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አራት ጎል ያስቆጠረው ተጫዋች ከጎል ጋር ካለው ግንኙነት በተጨማሪ ከኳስ እና ከኳስ ውጪ የሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች ለቡድኑ ጠቃሚ ናቸው።

በአዳማ ከተማ በነበረው ውድድር መልካም የሚባል ውጤት ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ባሳለፍነው ሳምንት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ በመከላከያ ሽንፈት አስተናግዷል። በጨዋታው መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ ባያደርግም በቅርብ ጨዋታዎች እየታዩበት የሚገኙት የመከላከል ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈሉት ይታሰባል። በመከላከያው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በቀደሙት አራት ጨዋታዎችም በድምሩ አስራ አንድ ግቦችን ለተጋጣሚ የፈቀደው ስብስቡ ይህንን ክፍተቱን በቶሎ መጠገን የግድ ይለዋል። እንደ መከላከያ የመውረድ ስጋት ያለበትን እና ከፊቱ ያሉበትን ጨዋታዎች የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባው ድሬዳዋን መግጠሙ ደግሞ ነገም ፈተናውን የሚያጠነክርበት ይመስላል። ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት በመጠቀም ለማጥቃት እንዲሁም ከአማካይ መስመር ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን እንዲያደርጉ የሚበረታቱ ተጫዋቾችን የያዘው ሀዲያ ነገም አጨዋወቱን በመከላከል ላይ መሰረት አድርጎ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚታሰበውን ድሬ ለማስከፈት እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንደሚጥር ይገመታል።

ድሬዳዋ ከተማ ያሲን ጀማልን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ በዚህም ሳምንት ግን የዳንኤል ኃይሉን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት ያጣል። ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ግርማ በቀለ እና ተስፋዬ አለባቸው በአምስት ቢጫ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑበት ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ የማይሰለፍ እንደሆነ ተነግሮናል።

የዕለቱን የመጀመሪያ ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ ከመስመር ረዳት ዳኞቹ ማንደፍሮ አበበ እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኘው ሚካኤል ጣዕመ እና ተጨማሪ የጎል አጠገብ ዳኞቹ አሸብር ታፈሠ እና ኤፍሬም ገብረማርያም ጋር ይመሩታል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ድሬዳዋ ከተማ አና ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሆሳዕና 2 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ አንድ አሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሆሳዕና 8 ፣ ድሬዳዋ 5 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ – ሱራፌል ጌታቸው

ማማዱ ሲዲቤ – ሄኖክ አየለ – ጋዲሳ መብራቴ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ያሬድ በቀለ

ቃለዓብ ውብሸት- ፍሬዘር ካሣ – ሔኖክ አርፌጮ

ብርሃኑ በቀለ – አበባየሁ ዮሐንስ – ኤፍሬም ዘካሪያስ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ኢያሱ ታምሩ

ዑመድ ኡኩሪ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ አስር ነጥቦች ዝቅ ብሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ድሉን ከቀጥተኛ ላለመውረድ ተፎካካሪው ጅማ ለማገኘት ወሳኝ ግጥሚያ ያከናውናል። እንዳለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ ረገድ ተጋጣሚው ሀዋሳን በመብለጥ ሲጫወት የተስተዋለው ሰበታ ከተማ በሁለቱም አጋማሾች በብዙ መስፈርቶች የተሻለ ቢሆንም ጎል ፊት ካለው አይናፋርነት መነሻነት ፍሬያማ ሳይሆን ቀርቷል። በተለይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች የነበራቸው የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ቡድኑን እጅጉን ጎድቶት ነበር። ለወትቶ በመከላከሉ ረገድ የማይታማው ሀዋሳ ላይ በድምሩ 20 ጊዜ ሙከራ በማድረግ ለማስከፈት ቢሞክርም በጠቀስነው ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። ነገ ደግሞ እየራቃቸው ከሚገኘው ጅማ ጋር በመጫወታቸው ውጤቱ እጅጉን ያስፈልጋቸዋል። ጅማም ከእነርሱ በመቀጠል ሁለተኛው ብዙ ግብ የተቆጠረበት ክለብ ስለሆነ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገራሉ ብሎ መናገር ባይቻልም ዕድሎችን የመጠቀም ጉዳይ ላይ ግን በአፅንኦት መስራት አለባቸው። በዋናነት ደግሞ ከመስመር የሚነሱት ጥቃቶች ዋጋቸው ከፍ የሚል ይመስላል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማግኘት ነገ ወደ ሜዳ የሚገባው ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ወቅታዊ ብቃቱ በጥሩ ውጤት የታጀበ ነው። ሁለት ጊዜ ብቻ ከአንድ በላይ ግብ አስቆጥሮ የሚያቀው ቡድኑም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አጥብቆ የሚፈልገውን ድል ሲያገኝ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ነው። እርግጥ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎችም በእንቅስቃሴ ደረጃ ለትችት የሚዳርግ ነገር ባያስመለክትም ውጤት መያዝ ተስኖት ነበር። በባህር ዳር እና አርባምንጭ ጨዋታ ግን እንቅስቃሴውን በውጤት አሳጅቦ ወጥቷል። በጊዜያዊ አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊ የሚመራው ጅማ ባሳለፍነው ሳምንት አርባምንጭን ሲረታ ከመመራት ተነስቶ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ ጨዋታው የገባበት መንገድ የሚያስደንቀው ነው። በኳስ ቁጥጥርም በግብ ሙከራም ተሽሎ ታይቷል። ነገ ደግሞ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚገመተውን ጨዋታ ባደገ እንቅስቃሴ እንደሚቀርብ ይገመታል። በተለይ ደግሞ በማጥቃት ላይ ያለው መሻሻል ከቅጣት መልስ የሚመጣውን መሐመድኑር ናስር ማግኘቱ ሲታወስ የፊት መስመሩ ለሰበታዎች አደጋ እንደሚሆን ያመላክታል።

ሰበታ ከተማ እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በነገው ጨዋታም ምንተስኖት ዓሎን በጉዳት ፍፁም ገብረማሪያምን በግል ጉዳይ ምክንያት እንደሚይጠቀም ታውቋል። ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ መሐመድኑር ናስር ከቅጣት መልስ ሲመለስለት ስብስቡ ውስጥ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለ ተመላክቷል።

ዓለማየሁ ለገሰ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ሰለሞን ተስፋዬ እና ተከተል በቀለ የመስመር ረዳት ምስጋናው መላኩ አራተኛ እንዲሁም ክንዴ ሙሴ እና ድሪባ ቀነኒሳ ደግሞ የጎል አጠገብ ተጨማሪ ዳኞች እንደሆኑ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ለ3 ጊዜያት ተገናኝተው ሰበታ 2 ሲያሸንፍ ፣ አንድ ጊዜ አቻ ተሌኣይተዋል። ሰበታ 4 ፣ ጅማ 2 አስቆጥረዋል

ግምታዊ አሰላለፍ


ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ዴሪክ ኒስባምቢ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

አላዛር ማርቆስ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ

መስዑድ መሀመድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – አድናን ረሻድ

ኢዮብ ዓለማየሁ – መሐመድኑር ናስር – ሱራፌል ዐወል

አዳማ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ድል ካደረገ ስምንት የጨዋታ ሳምንቶች ያስቆጠረው አዳማ ከተማ ቀስ እያለ እየተንሸራተተ ለደረጃው ግርጌ እየቀረበ ይገኛል። በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ከተጋጣሚ ሲያንስ የማይታየው ቡድኑ ከውጤት ጋር መገናኘት ተሳነው እንጂ እንቅስቃሴው መልካም ነበር። በ22ኛ ሳምንትም በሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለምንም ሲረታ በብዙ መመዘኛዎች የተሻለው ቡድን ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ማስተናገዱ እና የተፈጠሩ እድሎችን አለመጠቀሙ እንደ ክፍተት ሊነሳበት ይችላል እንጂ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ ነበር። እግር ኳስ ደግሞ ከውጤት ጋር የተገናኘ ስለሆነ ከድል ጋር በቶሎ መታረቅ የግድ ይለዋል። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች በንፅፅር ቀለል የሚል ተጋጣሚ ነገ መግጠሙ ደግሞ ወደአስፈላጊው መንገድ እንዲገባ ሊረዳው ይችላል። ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ አጨዋወት የሚከተለው ቡድኑ በቁጥር በርከት ብሎ የሚከላከለውን የአርባምንጭ የኋላ መስመር ለመክፈት ሜዳውን አስፍቶ መጫወት የሚያስፈልገው ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን እስካሁን ከአንድ ጎል በላይ ሁለት ጊዜ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ከአርባምንጭ ጋር ተጫውቶ በርካታ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ዕድሉ የጠበበ ስለሆነ የሚገኙ አጋጣሚዎችን መጠቀም የግድ ይላል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ እንደ አዳማ ከአስጊው ቀጠና ብዙም ስላራቀ የነገውን ውጤት አጥብቆ ይፈልገዋል። ይህንን ለማሳካት ግን በጅማ ሁለት ለአንድ ሲረታ ያሳየውን ብቃት ማሻሻል ይገባዋል። በተለይ ከኳስ ውጪ ያለውን አደረጃጀት በይበልጥ ማሳደግ ይጠበቅበታል። በመጀመሪያዎቹ 17 ጨዋታዎች አንድ ጊዜም ቢሆን ከአንድ በላይ ግብ አስተናግዶ የማያቀው ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ሁለት፣ ሦስት እና አራት ግብ አስተናግዷል። ጠንካራ ጎኑ ከኳስ ውጪ ያለ የቦታ እና የጊዜ አጠቃቀም ለሆነ ቡድን ደግሞ ይህንን የመከላከል አጨዋወት ያለ ምንም የትኩረት ማጣት መከወን ይገባል። ከዚህ ውጪ በሀዲያው ጨዋታ አራት ግብ ካስቆጠረ በኋላ ባሉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ ከወገብ በላይም እንደሳሳ ያመላክታል። ነገ የሊጉ ሁለተኛው ጥቂት ግቦችን ያስተናገደውን ቡድን እንደመግጠማቸው ደግሞ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው መናገር ያስፈልጋል። ሽግግሮች፣ የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች ደግሞ ዋነኛ የግብ ማግቢያ ምንጭ እንደሚሆኑ ይታሰባል።

አዳማ ከተማ ተከላካዩ አዲስ ተስፋዬን በቅጣት ምክንያት ሲያጣ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በጉዳት የሚያጣው ብቸኛ ተጫዋች ተከላካዩ አንድነት አዳነን ብቻ ነው። ልምምድ የጀመረው አህመድ ሁሴን ግን በነገው የአዞዎቹ ስብስብ ውስጥ እንደሚኖር ተጠቁሟል።

ዮናስ ካሣሁን ከረዳቶቹ ካሣሁን ፍፁም እና አያሌው አሰፋ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ተስፋዬ ጉርሙ እና የጎል አጠገብ ዳኞቹ ሸዋንግዛው ተባበል እና አብዱ ይጥና ጨዋታውን ይመሩታል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አዳማ እና አርበምንጭ 13 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 5 አዳማ 4 አሸንፈው 4 አቻ ተለያይተዋል። አርባምንጭ 11 እና አዳማ 10 ጎል አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩምባ ካማራ

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – ሚሊዮን ሰለሞን – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – ማርቲን ኦኮሮ – በርናንድ ኦቼንግ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ፀጋዬ አበራ

ኤሪክ ካፓይቶ – በላይ ገዛኸኝ

ያጋሩ