የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 4-0 ሀዲያ ሆሳዕና

ረፋድ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ስጋት ፈቀቅ ካለበት ድል በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለዛሬው አጨዋወት

“ ዛሬ የተለየ ነው። በተለይ ይዘነው የመጣነውን የጨዋታ አቀራረብ ልጆቹ በአግባቡ በመወጣታቸው የተሳካ ነው ማለት ይቻላል። መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ እንደሚወስዱብን እናውቅ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ከግራ እና ከቀኝ የሚለቋቸውን ቦታዎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ልጆቼ ውጤታማ ነበሩ። ከዚህ ውጪ በባለፈው ጨዋታ ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ችግሮችን ዛሬ ከሞላ ጎደል እጅግ የተሻለ ነበር።

ስለ መጀመርያ ሁለት ጎሎች ወሳኝነት

“በጣም ትክክል፣ የጨዋታው ውጤት የሚወስን ነበር። ሁለተኛው ጎል ተጋጣሚያችንን እንዲወርድ ነው ያደረገው። ለእኛም መጠነኛ ጉልበት እንዲኖረን ያደረገ ከመሆኑ አንፃር በጣም ጥሩ ነበር።

ስለመውረድ ስጋት

“የስጋቱን መጠን ሊቀንስ ይችላል። ሙሉ ለሙሉ ግን ወጥተናል ብሎ መናገር አይቻልም ፤ ገና ነው። የምንጨርሳቸው ነገሮች አሉ። ከፊት እዚህ ቀጠና ላይ የሚገኙ ሁለት ቡድኖች አሉ እነርሱን ካሸነፍን በኋላ ነው ወደ አስተማማኝ ደረጃ ሄደናል ብለን መናገር የምንችለው።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለተወሰደባቸው ብልጫ

“እነርሱ ለእኛ ኳሱን እንድንጫወት ለቀውልናል። ግን የመጨረሻው ቦታ ላይ እነርሱን ልናገኛቸው አልቻልንም። ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ ጎል አግብተውብናል። ከእኛም ተሽለው ስለነበረ ጎል በማስቆጠራቸው ዛሬ ተቀብለናል።

ጎል ማስቆጠር ስለመቸገራቸው

“ይሄ በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው። የሚገባበት ጊዜ አለ፣ የማይገባበት ጊዜ አለ። ከዚህ ቀደም ካስተዋልን ከአንድ አንድ ፣ ከሁለት ሁለት ሄደን እናገባ ነበር። ዛሬ ግን አልተሳካልንም ፤ ዛሬ የእኛ ቀን አይደለም። ዛሬ የድሬዳዋ ቀን ነው። ምንም ማለት አልችልም። እነርሱን እንኳን ደስ ያላችሁ ነው የምለው። የሀዲያ ደጋፊዎችን ደግሞ ይቅርታ እንጠይቃለን። እናሻሽላለን ነው የምለው።”