የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-1 ጅማ አባ ጅፋር

ቀትር ላይ ሁለቱ በመውረድ ስጋት ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በሰበታ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ውጥረት የተሞላበት ነበር። ከፈጣሪ ጋር ይህችን ሦስት ነጥብ ልናገኝ ችለናል።

ጎል ስለማስቆጠራቸው

“ ጎል ለማስቆጠር የቻልነውን በማድረግ ፍፁም በሆነ ትጋት ውስጥ ገብተናል። ተነጋግረንም ነበር ፤ የምናገኛቸውን ዕድሎች በሙሉ ወደ ጎልነት ለመጨረስ በብርቱ አዕምሮ ስንሰራ ነበር። ተሳክቶልን ሁለት ጎል አስቆጥረን ለማሸነፍ በቅተናል።

ድሉ የዘገየ ነው

“የዘገየ ድል ነው ማለት ይቻላል። ቢዘገይም ደግሞ አሁን ከፊት ለፊት ያሉንብን ጨዋታዎች እንዲሁ ተጠናክረን ለማሸነፍ እንሄዳለን። በምንም መልኩ ግን ሳንዘናጋ ቡድናችንን ወደ ታች አናደርገውም። ስሜታችንን ከፍ ነው የምናደርገው።”

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለሽንፈቱ ምክንያት

“የመጀመርያው 45 ደቂቃ ከአስር ደቂቃ በኋላ የመጫወት ፍላጎታችን ጥሩ አልነበረም። ጎሉን ካስቆጠርን በኋላ እንቅስቃሴያችን በምንፈልገው ደረጃ አላገኘነውም። ሁለተኛው አጋማሽም እንዳያችሁት ተደጋጋሚ ጎል ጋር ሄደናል ያገኘነውን አጋጣሚ አልተጠቀምንም።

ትኩረት ስለመስጠት

“ትኩረት ሰጥተነዋል ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ከሆነ እኛ አልተሳካልንም እንጂ በምንፈልገው ነው የተጫወትነው።

ሽንፈቱ ስለሚኖረው ተፅዕኖ

” ያው ጨዋታው ይቀጥላል ፤ ተፅዕኖም ይፈጥራል። ባለን አማራጭ የተሻለ ነገር ለማምጣት እንቀጥላለን።”