በጨዋታ ሳምንቱ በሰንጠረዡ ግርጌ ትልቅ ትርጉም በነበረው ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 በማሸነፍ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሚባል ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
ሰበታ ከተማዎች ከሀዋሳ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ዱሬሳ ሹቢሳን በቢስማርክ አፒያ ምትክ በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።
በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ አርባምንጭን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው አራት ለውጦች የዓብስራ ሙሉጌታ ፣ ዳዊት ፍቃዱ ፣ እዮብ አለማየሁ እና አስጨናቂ ፀጋዬን አስወጥተው በምትካቸው ወንድማገኝ ማርቆስ ፣ ሙሴ ካበላ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና መሀመድ ኑር ናስር አስገብተዋል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረው ገና በማለዳ ነበር ፤ በ7ኛው ደቂቃ ሽመልስ ተገኝ በሁለት የሰበታ ተከላካዮች ጀርባ ያሾለከለትን ኳስ ተጠቅሞ ወጣቱ አጥቂ መሀመድ ኑር ናስር በግሩም አጨራረስ ከሳጥኑ ጠርዝ ባስቆጠራት ግብ አባ ጅፋሮች ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
በግቧ መቆጠር ያልተረበሹት ሰበታ ከተማዎች በተለይ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች በተደጋጋሚ ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል ፤ በ6ኛው እና በ11ኛው ደቂቃ ዱሬሳ ሹቢሳ ያደረጋቸው እንዲሁም በ15ኛው ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳሳ ሳሙኤል ሳሊሶ ከአላዛር ማርቆስ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ። ይህ ጥረታቸው በ20ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ አስገኝቷል ፤ ጋብርኤል አህመድ ከተከላካይ ጀርባ በጣለው ኳስ በጀመረው የማጥቃት ሂደት ጌቱ ኃይለማርያም ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ኳስ ዲሪክ ንሲምባቢ በግንባሩ ገጭቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
34ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ሂደት ጉዳት ያስተናገደው እና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሰበታ ከተማዎች በኩል ጥሩ ሲጥር የነበረው ሳሙኤል ሳሊሶ በጉዳት ምክንያት መቀጠል አለመቻሉን ተከትሎ በዘካርያስ ፍቅሬ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
ከአቻነቷ ግብ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሰበታ ከተማዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እንዲሁም እንደተለመደው ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ36ኛው ደቂቃ ላይ ጋብርኤል አህመድ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ዴሪክ ንሲምባቢ ያደረገው እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣበት አደገኛ ሙከራ ነበር። በአንፃሩ በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በአጋማሹ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው ዳግም ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም አጋማሹን በ47ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቆመ ኳስ ባደረገው አደገኛ ሙከራ ፈፅመዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅምሩ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች በአጋማሹ ጅማሮ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ደቂቃዎች ፍፁም ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን በአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ጌቱ ሃይለማርያም አማካኝነት ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። የሰበታን ማጥቃት ለመቋቋም በጥልቀት ለመከላከል የተገደዱት ጅማዎች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ሰበታን ለመጉዳት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተለይም 53ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋፎች ፈጥን ባለ የመልሶ ማጥቃት አድናን ረሻድ እና መሀመድ ኑር ናስር በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል ሰበታ ከተማ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ መሀመድ ኑር የሞከረው አደገኛ አጋጣሚ ለዓለም ብርሃኑ አድኖባቸዋል።
ከፍ ያለ ጫና አሳድረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሰበታ ከተማዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል። በ60ኛው ደቂቃ ዱሬሳ ሹቢሳ ከግራ መስመር ወደ ጅማ ሳጥን ለመድረስ ባደረገው ጥረት በሽመልስ ተገኝ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አብዱልሀፊፍ ቶፊቅ አስቆጥሮ ሰበታ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ በኋላም ቢሆን ሙሉ ሦስት ነጥቡን ለማግኘት ሲታትሩ የነበሩት ሰበታዎች በ67ኛው ደቂቃ ላይ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከተከላካይ ጀርባ ሾልኮ ያደረገው እና አላዛር ያዳነበት እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዘካርያስ ፍቅሬ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ግን ጅማ አባ ጅፋሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በቻሉት አቅም ሁሉ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል። በዚህም ሁለት አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ትልቅ ዋጋ የነበረውን ጨዋታ በበላይነት ያጠናቀቁት ሰበታ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 17 በማሳደግ ከበላያቸው ከሚገኘው ጅማ አባጅፋር ጋር ልዮነቱን ወደ ሁለት ነጥብ ማጥበብ ችለዋል።