ነገ በሚደረጉት የሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ
ይህ ጨዋታ በአዳማው ውድድር መጀመሪያ ላይ ቢሆን የበለጠ ከፍ ያለ ትርጉም ይኖረው ነበር። ከዛ ጊዜ አንስቶ ፍጥነቱን የጨመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ከነገ ተጋጣሚው 15 ነጥቦች ርቆ ተቀምጧል። ወደ ዋንጫው የሚያደርገውን ጉዞ ለመቀጠልም ነገ በሙሉ አቅም ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በቅርብ ሳምንታት ከነገ ተጋጣሚያቸው በተቃረነ ጊዜ ውስጥ ያለፉት ወላይታ ድቻዎች አንድ ነጥብ ካሳኩበት ጨዋታ መልስ ነው ጊዮርጊስን የሚያገኙት። ቡድኑ ከሁለተኛ ደረጃም በአምስት ነጥቦች በመራቁ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ውጤት ይዞ ልዩነቱን ማጥበብ ይጠበቅበታል።
ጨዋታዎችን አሸንፎ የመውጫ አማራጮቹ በርካታ እንደሆኑ በየሳምንቱ እያሳየ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጎል የማግኘት ማላ የማያጣ ቡድን ሆኗል። በድምሩ 15 ጎሎች ያስቆጠሩለት ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ እና አቤል ያለው በሌሉባቸው ጨዋታዎች በተለያዩ የሜዳ ክፍል ላይ ከሚገኙ ተሰላፊዎቹ ግቦችን ማግኘት መቻሉ የቡድኑ የውጤት ቁልፍ ሆኖ ታይቷል። በተለይም ከክፍት ጨዋታ ዕድሎችን መፍጠር ከባድ በሚሆኑበት አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች ደጋግሞ ግብ ማስቆጠሩ በዚህ ረገድ የሚነግረን ነገር አለ። ይህ ነጥብ አስፈላጊ ሲሆን በራሱ የግብ ክልል ችምችም ብሎ ለመከላከል ወደ ኋላ ለማይለው የነገ ተጋጣሚያቸው ላይ ሊረዳቸው የሚችል ጠንካራ ጎናቸው ነው። ቡድኑ እነዚህን መንገዶች ባጣባቸው ጨዋታዎች ያለግብ ሲጨርስ መታዘባችን ግን በቅብብሎች ክፍተቶችን የመፍጠር አቅሙን ከፍ አድርጎ መምጣት የነገ ፈተናው ሊሆን እንደሚችል እንድንገምት ያደርጋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድናቸው ሦስት ግብ ካስተናገደበት የፋሲሉ ጨዋታ መልስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር መረቡን አለማስደፈሩ ለነገው ጨዋታ የሚወስዱት መልካም ነገር ነው። የአንተነህ ጉግሳ እና መልካሙ ቦጋለን ጥምረት በአንተነህ እና ደጉ ደበበ ጥምረት በተኩበት ጨዋታ ኳስ ለሚይዘው ተጋጣሚያቸው ክፍተት ያልሰጡበትን አኳኋን ነገም በጨዋታ ዕቅዳቸው ውስጥ እንደሚከቱት ይታሰባል። ከዚህ ባሻገር ድቻዎች ከነገው ጨዋታ ክብደት አንፃር የሦስት ተከላካዮች ጥምረትን ሊተገብሩም ይችላሉ። ሆኖም ግን ትልቁ የቤት ሥራቸው የሚሆነው ከስንታየሁ መንግሥቱ ጉዳት በኋላ ግብ ማምረት የተሳነው የፊት መስመራቸው ነው። በውድድር ዓመቱ ሰባት ግቦች ብቻ ካስተናገደው ተጋጣሚያቸው የኋላ መስመር ጥንካሬ አንፃር በተለይም በመልሶ ማጥቃት ወቅት የአጥቂዎቻቸውን አፈፃፀም ማሳደግ አልያም በውድድሩ አጋማሽ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብነት የመለወጥ ፎርሙላ መልሰው ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋቶች ፓኖም ከቅጣት ሲመለስለት ጉዳት ላይ የሰነበተው አቤል ያለው ግን ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ተሰምቷል። በወላይታ ድቻ በኩል ፅዮን መርዕድ በአምስት ቢጫ ካርዶች ቅጣት እንዲሁም ስንታየሁ መንግሥቱ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 7 ጊዜ ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) አምስቱን ድል አድርጓል። ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 20 ጎሎች ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ ደግሞ (ሦስት የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) 13 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ
ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም
የአብስራ ተስፋዬ – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ
አማኑኤል ገብረሚካኤል
ወላይታ ድቻ (3-5-2)
ወንድወሰን አሸናፊ
በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ
ያሬድ ዳዊት – ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ – አናጋው ባደግ
ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ
04:00 ሲል የሚጀምረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር አፍቃሪዎቹ ቡድኖች መካከል ሲከናወን ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደሚደረግበት ይጠበቃል። ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና ቢያንስ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ደረጃው ለመፋለም ከበላዩ ካሉት ቡድኖች ጋር ያለውን ልዩነት በዚህ ጨዋታ ማጥበብ ይጠበቅበታል። የሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ወልቂጤዎች ደግሞ ከታች ያለው የነጥብ መቀራረብ እንዳይስባቸው ነጥባቸውን ከ30 በላይ ለማሻገር የነገውን ውጤት ይፈልጉታል።
ኢትዮጵያ ቡና በድሬዳዋው ጨዋታ የዋነኛ አጥቂው አቡበከር ናስርን ተፈላጊ አቋም ማግኘት ችሎ ነበር። አቡበከር ካስቆጠራቸውም ግቦች ውጪ በነበረው እንቅስቃሴም ኢትዮጵያ ቡና አጥቶት የነበረውን እና በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን አስፈሪነት መላበስ ችሎ ነበር። በእርግጥ ተጫዋቹ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ አገግሞ እየተጫወተ ነው ለማለት ቢከብድም የእርሱን መኖር ተከትሎ በተጋጣሚ ተከላካዮች አቋቋም ላይ የሚፈጠሩ መዘበራረቆችን ለመጠቀም መጣር ይኖርበታል። በተለይም በነገው ጨዋታ በጥልቅ የማይከላከለውን እና በተመሳሳይ ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወተውን ወልቂጤን ሲገጥም የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ውስጥ የሚተዉትን ቦታ ለመጠቀምም ሆነ በመስመሮች መካከል ለመግባት እንደ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ዊሊያም ሰለሞን ዓይነት ተጨዋቾች በቀደመ ጥሩ ብቃታቸው ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል።
ወልቂጤ ከተማ በ21ኛው ሳምንት ከገጠመው አዲስ አበባ ከተማ የተለየ ተጋጣሚ ያገኘዋል። በዛ ጨዋታ ከኳስ ጋር ሲሆን ምቾት አይሰጠው ከነበረው የመዲናዋ ክለብ አንፃር ለቀቅ ያለ የአማካይ ክፍል ፍልሚያ ሊሆንላቸው ይችላል። የቡድኑ አማካዮች ከኳስ ውጪ በትጋት ጫና አስድሮ ክፍተቶችን የመድፈን የከዚህ ቀድመ ብቃታቸው ነገ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና አቻዎቸው በተሻለ የኳስ ስርጭት ደረጃ ላይ መገኘት መቻል ደግሞ ዋነኛ የቤት ስራቸው ይሆናል። በዚህም ውስጥ ለጥቃት በመያጋለጥ መልኩ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች እገዛ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም። ቡድኑ ባለው ጠንካራ ጎን የኳስ ቁጥጥሩን በተጋጣሚ ሜዳ ውስጥ ማዝለቅ ከቻለ ጌታነህ ከበደ በሳጥኑ ዙሪያ ኳስ በሚያገኝባቸው አጋጣሚዎች ከሚወስናቸው አደገኛ ውሳኔዎች እና ከጫላ ተሺታ ፍጥነት እና ቦታ አያያዝ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
ተጋጣሚዎቹ የቅጣት ዜና የሌለባቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ወንድሜነህ ደረጀ ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ቴዎድሮስ በቀለን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አበባው ቡታቆን በጉዳት ያጣሉ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዓምና ጀምሮ ሦስት የግንኘነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተው ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ጊዜ ድል አድርጓል። በጨዋታዎቹ ቡና 5 ፣ ወልቂጤ ደግሞ3 ግቦች አሏቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – ስዩም ተስፋዬ
ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሠ ሰለሞን
ዊሊያም ሰለሞን – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ሮበርት ኦዶንካራ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
ያሬድ ታደሠ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ