ሪፖርት | በትንኞች የተወረረው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ያለ ግብ የተለያዩት አዳማ እና አርባምንጭ በጋራ 26ኛ የአቻ ውጤታቸውን አስመዝግበዋል።

አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት መልስ ዛሬ ቶማስ ስምረቱን በአዲስ ተስፋዬ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። በጅማ አባ ጅፋር ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጮች ባደረጓቸው አራት ለውጦች ደግሞ ይስሀቅ ተገኝን በሳምሶን አሰፋ ፣ ሙና በቀለን በአሸናፊ ኤልያስ ፣ ሀቢብ ከማልን በፀጋዬ አበራ እንዲሁም ፍቃዱ መኮንን በበላይ ገዛኸኝ ምትክ በማስገባት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

አዳማ ከተማ የተሻለ ወደ ፊት የመሄድ ምልክት ቢያሳይም ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር በነበረው ጨዋታ 12ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጓል። ዳዋ ሆቴሳ ከዮናስ ገረመው የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ አጠንክሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል። አዳማ ከተማዎች ቀስ በቀስ በትዕግስት ኳስ መስርተው ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። ያም ቢሆን በጥልቀት እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ ያሰቡት አርባምንጮች የሚቀመሱ አልሆኑም።

አንዳቸው የሌላኛቸውን የማጥቃት ጥረት እያቋረጡ የቀጠለው ጨዋታ ወደ ሁለቱም ግቦች ያነጣጠሩ የቆመ ኳስ አጋጣሚዎች በርከት ብለው ቢታዩም አንዳቸውም ግብ ጠባቂዎቹን መፈተን አልቻሉም። 25ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመው አጥቂያቸው ፍቃዱ መኮንን በፀጋዬ አበራ የተኩት አርባምንጮች ተጋጣሚያቸው ሰርጎ እንዳይገባ ቢያደርጉም ደካማ የማጥቃት ሽግግር ነበራቸው። የአዳማ የኳስ ቁጥጥር ወደ ፊት በመሄዱ በኩል ወደ መጨረሻው ላይ ቢሻሻልም ይስሀቅ ተገኝን ካልፈተኑ የአማኑኤል ጎበና እና አቡበከር ወንድሙ የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ውጪ የተሻለ ዕድል አልፈጠሩም።

ከዕርፍት መስል ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ከእንቅስቃሴው ይልቅ በሜዳው ላይ ተበራክተው ተጫዋቾች ፣ ዳኞች እና አሰልጣኞችን የፈተኑት ትንኞች ትኩረትን ይስቡ ነበር። አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥራቸው ይበልጥ ከተጋጣሚ ሜዳ ርቆ የመልሶ ማጥቃት ባህሪ ሲታይባቸው የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ግን እጅግ ደካማ ነበሩ። አርባምንጮች በአንፃሩ በጥቂቱ በተሻለ ሁኔታ ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ጀምረዋል። በዚህም ባደረጉት ሙከራ 66ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከሳጥን ውጪ ያደረገው የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ሲመለስ ሀቢብ ከማል በድጋሚ ወደ ግብ ልኮት ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከዚህ ሙከራ በኋላ በጨዋታው አስደንጋጭ ሁኔታ ሲፈጠር ተካልኝ ደጀኔ እና አቡበከር ወንድሙ ለአየር ላይ ኳስ በተሻሙበት ወቅት ተጋጭተው ከባድ አደጋ አስተናግደዋል። ለአምስት ደቂቃዎች ጨዋታውን ባቋረጠው በዚህ ክስተት በተለይም የአርባምንጭ ከተማው ተካልኝ ደጀኔ ተጨማሪ የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ አቡበከር ወንድሙም እንዲሁ ተቀይሮ ወጥቷል።

ጨዋታው ካቆመበት ሲቀጥል ፀጋዬ አበራ በድጋሚ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጎ የተመለከትን ቢሆንም ተደጋጋሚ ግጭቶች እና ጉዳቶች ጨዋታውን መልሰው አቀዛቅዘውታል። ባልተሳኩ የማጥቃት ጥረቶች የቀጠለው ጨዋታ 8 ደቂቃዎች ቢጨመሩበትም በከባድ ሙከራ ደረጃ የሚጠቀስ እንቅስቃሴ እንኳን ሳይታይበት 0-0 ተጠናቋል።

በውጤቱ ሁለቱ ቡድኖች ነጥባቸው 27 ላይ እንዲገደብ እና ከወራጅ ቀጠናው እንዳይርቁ ሆነዋል።

ያጋሩ