የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 አርባምንጭ ከተማ

አዳማ እና አርባምንጭ ያለ ጎል ከፈፀሙት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“በመጀመሪያው አርባ አምሰት ጥሩ ነበርን፡፡ በሁለተኛው አርባ አምስት ግን ወጣ ገባ የማለት ነገር ነበር፡፡ ከሜዳችን መስርተን እንዳንወጣ ተፅእኖ ለማድረግ እየሞከሩ ነበር፡፡ እንደ ጨዋታ የመጀመሪያው አርባ አምስት የተሻለ ነው፡፡ ሁለተኛው አርባ አምስት ትንሽ በውጥረት እና በጭንቀት የተወጠረ ጨዋታ ነው፡፡ ጎል ለማግኘት ስለፈለግን የምንፈልገውን ውጤት አላገኘንም፡፡

የአቻ ውጤቱ 15 ስለ መድረሱ

“አስቸጋሪ ነው፡፡ በእግር ኳስ እንዲህ ዓይነት ነገር አንዳንዴ ያጋጥማል፡፡ ሁልጊዜ እንደምለው ነው፡፡ ሜዳ ላይ ጥሩ ቡድን ነው ያለን፡፡ ያንን ወደ ውጤት መቀየር ነው ያቃተን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብዙ የጎል ዕድሎችን እናገኛለን አንጠቀምም ፤ ግልፅ ናቸው፡፡ እነርሱን አግኝተን ኮንፊደንሳችንን ከፍ ካላደረግን እና ወደ ማሸነፍ እስካልመጣን ድረስ ፣ ተጫዋቾቻችን ፣ እኛም የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ፣ ጫና ውስጥ ሆነን መቀጠላችን የማይቀር ነው፡፡”

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ነበረው የኃይል አጨዋወት

“ቅድም መጀመሪያ ስንጀምር እንዳልኩት ካለንበት ስፍራ መውጣት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ትንሽ ስሜት ያለበት ጨዋታ መጫወት ይፈልጋል ፡፡ ሞራል ያስፈልጋል ፤ ለዚህም ንክኪዎች ይኖራሉ፡፡ በእነዛ ንክኪዎች ደግሞ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የምንፈልገውን ብልጫ ወስደናል፡፡ ከሞላ ፣ ጎደል ጨዋታውን እኛ ወደምንፈልገው ወስደናል፡፡

ስለ ዘጠና ደቂቃው ቆይታ

“ይቀረናል፡፡ በፈለግነው መልክ ሄደናል ማለት አልችልም፡፡ ከዚህ በላይ መሻሻል መቻል አለብን፡፡ ለማሸነፍ አሁን ካለን በላይ ፐርፎርም ማድረግ አለብን፡፡”