የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ የሚቀረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የምድብ ሀ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አዳማ ከተማ ድል ሲቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት ሊካሄድ የነበረው የሀላባ ከተማ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በርበሬዎቹ ጎንደር ላይ በተካሄደው የመጀመርያው ዙር ውድድር ተሳትፎ ያደረጉ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ውድድር ላይ በፋይናስ ዕጥረት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ ለእያንዳንዱ ቡድን ፎርፌ እየተሰጠ በመሆኑ የዛሬው ተጋጣሚ ወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎል በማግኘቱ የነገውን ጨዋታ ሳይጨምር ነጥቡን ወደ ሠላሳ ሦስት በማድረስ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።

ስምንት ሰዓት በተካሄደው ጨዋታ አደማ ከመራት ተነስቶ አርባምንጭን 2-1 ማሸነፍ ችሏል

አርባምንጭ ጎሉን አስካስቆጠረበት 34ኛው ደቂቃ ድረስ በአዳማ በኩል ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ጀምረው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በአግባቡ ለተገቢው የአጥቂ ተጫዋቾች ኳሱ የማይደርስ በመሆኑ ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ አርባምንጮች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ከየትኛውም አቅጣጫ ኳስ እግራቸው ሲገባ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች የጎል ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም ዕብዛም የተሳካ አልነበረም። 

ሆኖም ግን አዳማዎች ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ሞክረው የተመለሰውን ኳስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር በረከት ሉቃስ ከወደ ሳጥን ያሻገረውን ግዙፉ አጥቂ ያሬድ መኮንን አግኝቶ በቀላሉ ወደ ጎልነት በመቀየር አርባምንጭን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተነቃቁት አዳማዎች በዮሐንስ ፈንታ የርቀት ኳስ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ምን አልባትም ጨዋታውን መቆጣጠር የሚችሉበትን የሁለተኛ ጎል ዕድል በመልሶ ማጥቃት አርባምንጮች በዘላለም ደጀኔ አማካኝነት አግኝተው ለመሳት በሚከብድ ሁኔታ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ያመከነው የሚያስቆጭ ነበር። ኳሱን ተቆጣጥረው በሚገኙ ክፍት ሜዳዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት አዳማዎች በ63ኛው ደቂቃ የአቻነት ጎል ማግኘት ችለዋል። ጎሉንም ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቢችልም የመሰለፍ ዕድል ያላገኘው የዓምናው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ኮከብ ተጫዋች ዮሴፍ ታረቀኝ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።
ቀዳሚውን ጎል ለአርባምንጭ ያስቆጠረው ያሬድ መኮንን የግል ጥረቱን በመጠቅም ሳጥን ውስጥ በመግባት በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ያዳነበት መልካም አጋጣሚ ነበር።

ጫና ፈጥረው በጨዋታው ሦስት ነጥብ ለመውሰድ በሙሉ አቅማቸው ከጨዋታ ብልጫ ጋር ማጥቃታቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በ71ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ወደ ጎልነት ቀይረውታል። ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት አብዲ ዋበላ በመምታት የአዳምን ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። 

በቀሪው ደቂቃ አርባምንጮች አቻ ለመውጣት ነቅለው በሚያጠቁበት አጋጣሚ አዳማዎች የሚያገኙትን ነፃ ቦታ በመጠቀም ተጨማሪ ጎል በዮሴፍ ታረቀኝ እንዲሁም አብዲ ዋበላ አግኝተው ሳይጠቀሙ በመቅረታቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማዎች በዛው ባሉበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲቆዩ አርባምንጭ ከተማ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሽንፈታቸውን በማስተናገድ በዛው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ፀንተዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የተመራው የአስር ሰዓቱ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል

ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሀዲያ ሆሳዕና ባገናኘው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በሁሉም ረገድ ኳሱን ተቆጣጥረው ብልጫ ወስደው ይጫወቱ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ያገኙትን አጋጣሚ አለመጠቀማቸው አስገራሚ ነበር። በተለይ በ12ኛው ደቂቃ በዋናው ቡድን ያደገው አጥቂው በረከት ብርሀኑ ቦታ አይቶ የመታው እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ፣ ራሱ በድጋሚ ከተከላካይ ጀርባ ተጥሎለት በፍጥነት ኳሱን አግኝቶ ቢገባም ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኤልፓዎች ያገኟቸው ግልፅ የጎል ዕድሎች ነበሩ። ከራሳቸው አጨዋወት ይልቅ ኤልፓዎች የሚፈጥሩትን ስህተት በመጠቀም በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ቢያስቡም በመጀመርያው አጋማሽ ሀዲያዎች የጠራ የጎል ሙከራ ሳያስመለክቱን ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ድካም የታየባቸው ኤልፓዎች በተደጋጋሚ በሀዲያዎች ግልፅ የጎል ዕድሎች ተፈጥሮባቸዋል። በተለይ በ55ኛው ደቂቃ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በቅብብል መሀል የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የሀዲያው አጥቂ ሳሙኤል ገረመው ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች። በሌላ አጋጣሚ የሀዲያው ሊሬ አባይነህ ከመስመር የተሻገረለት ነፃ ኳስ አግኝቶ በማይታመን መልኩ ያልተጠቀመበት አስገራሚ ሆኖ አልፏል። ያም ቢሆን ተቀይሮ የገባው ተመስገን ደነቀ በሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በ67ኛው ደቂቃ ወደ ጎልነት በመቀየር ሀዲያን ቀዳሚ አድርጓል።

ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ የሀዲያን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት ኤልፓዎች ከአስር ደቂቃ በኋላ ከቅጣት ምት ያገኙትን ኳስ በረከት ወደ ጎል ሲያሻማው ተቀይሮ የገባው ቢንያም በቀለ ኳሱን በመሽረፍ ቡድኑን አቻ አድርጓል። በቀሪ ደቂቃዎች ኤልፓዎች ጨዋታውን በተገቢው ሁኔታ ተቆጣጥረው ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ማሸነፍ የሚችሉበትን ዕድሎች ከአንዴም ሁለቴ አጥቂው በረከት ብርሀኑ ሳይጠቀም በመቅረቱ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኤልፓም ሀዲያም ወደ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመግባት ያላቸውን ዕድል ውስብስብ በማድረግ በዛው ባሉበት ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።

የዚሁ ምድብ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ በ08:00 ሰበታ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ እንዲሁም የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና 10:00 ላይ የሚደረግ ይሆናል።