ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ከጦና ንቦቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በዕለቱ ተጠባቂ በነበረው መርሐግብር መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር ጨዋታውን ያለግብ ፈፅሟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን ከረታው የመጀመሪያ 11 ባደረጋቸው ሁለት ለውጦች ናትናኤል ዘለቀ እና ሀይደር ሸረፋን በማሳረፍ በምትካቸው ጋቶች ፖኖም እና ቡልቻ ሹራ ሲተካ በአንፃሩ ከባህር ዳር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ በአምስት ቢጫ ምክንያት መሰለፍ ባልቻለው ግብ ጠባቂያቸው ፅዮን መርዕድ ቦታ ቢኒያም ገነቱን በመጠቀም ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ከጅማሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በጥልቀት ተስበው በመከላከል በተወሰነ መልኩ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ይህን የመከላከል አወቃቀር ለማስከፈት ሲታትሩ የተመለከትንበት ነበር።

በአጋማሹ በ14ኛው ደቂቃ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በድቻ ግብ ትይዩ ያገኘውን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው እና ቢኒያም በግሩም ቅልጥፍና ካዳነበት ኳስ ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩበት አጋማሽ ነበር። በዚሁ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በዚህም ሂደት በክፍት ጨዋታ ዕድሎችን ለመፍጠር ከመቸገራቸው የተነሳ በአጋማቹ ያሀኟችፕው አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች የተፈጠሩ ነበሩ። ነገር ግን ቢኒያም ገነቱን የፈተነ ሙከራ ሳንመለከት ቀርተናል።


በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች የተሻለ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች በ8ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም በ11ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራ የተሻሉ በአጋማሹ ያደረጓቸው ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ግን በጨዋታው የተሻለ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በተጋጣሚ አጋማሽ ከተነጠሉት አጥቂዎች ውጪ በቂ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻላቸው ሲመክኑ አስውለናል።
በ20ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በጨዋታው ከተወሰኑ ደቂቃዎችን አስቀድሞ አምስተኛ ቢጫ ካርዱን የተመለከተው ያሬድ ዳዊት ተቀይሮ እንዲወጣ በመወሰናቸው በአበባየሁ አጪሶ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል። በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ በአጋማሹ ጥሩ ሲጥር የነበረው ከነዓን ማርክነህ ትከሻው ላይ ባጋጠመው ጉዳት መነሻነት በሀይደር ሸረፋ በ43ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በመውጣት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።


በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሜዳውን አስፍቶ በመጫወት ረገድ የተሻለ ማገዝ የሚችለውን ሱሌይማን ሀሚድን በቀኝ መስመር ተከላካይነት ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። ይህም ጥረታቸው በፍጥነት ውጤት ማሳየት ጀምሯል። በ53ኛው ደቂቃ በግሩም ቅብብል ድቻ ሳጥን የደረሱትን ኳስ ሱሌይማን ሀሚድ የሞከረው እንዳሁም በ55ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር ያሻማውን አማኑኤል ገ/ሚካኤል ገጭቶ ቢሞክርም ሁለቱን ኳስ ቢኒያም ገነቱ በግሩም ሁኔታ አድኖባቸዋል።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ወላይታ ድቻዎች ቀስ በቀስ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለማጥቃት በርከተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መግባት መጀመራቸውን ተከትሎ በመልሶ ማጥቃት እጅግ አደገኛ አጋጣሚ ፈጥረዋል። 


በተለይም በ65ኛው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሂደት የተገኘውን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር ያደረሰውን ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ፍቅሬ አስቆጠረ ሲባል ለሉክዋጎ ያሳቀፈው እንዲሁም በ72ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ቢኒያም የመጀመሪያ ኳስ አሸንፎ ያቀበለውን ምንይሉ በግንባሩ ሲገጭ በተመሳሳይ ሉክዋጎ በቀላሉ ያዳናቸው አጋጣሚዎች ድቻን አሸናፊ ማድረግ የሚችሉ ነበሩ።
በጨዋታው ማጥቃታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም በ85ኛው ደቂቃ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ የተሻማውን ኳስ ተገጭቶ ሲመለስ ዳግማዊ ዓርአያ አስቆጠረው ሲባል ቢኒያም ገነቱ በፍጥነት የግብ ክልሉን ለቆ ያዳነበት ኳስ ለቡድኑ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን ወደ 51 አሳድገው መምራታቸውን ሲቀጥሉ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በ36 ነጥብ በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ያጋሩ