የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ወላይታ ድቻ

የረፋዱ ጨዋታ ያለ ጎል ከተገባደደ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ውጤቱ በዋንጫ ጉዞ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ

“ያው ስለተፅዕኖ ሳይሆን እያሸነፍን ብንሄድ የተሻለ ነገር ይኖራል። አሁንም ቢሆን መጥፎ ነገር ውስጥ አይደለንም። ግን ጨዋታውን እንደፈለግነው እና አቅደን እንደመጣነው አላገኘንም።

ክፍት ሜዳ ለማግኘት ስለመታገስ

“አዎ ብዙ ትዕግስት አድርገን ነበር። በመስመሮች ተጫውተን ለማስከፈት ፈልገን ነበር ፤ አልሆነም አልተሳካም። ከእነርሱ ጥንካሬ ፣ ከእኛ ስህተት ይሆናል። ቀላል ስህተቶች ማድረግ የሚኖርብንን ስላላደረግን አቻ ለመውጣት ተገደናል።

አንድ ለአንድ ስለመጋለጣቸው

“ያ ድክመት አይደለም። ጎል ለማግባት ሁሉም ነቅለው ስለሚወጡ በዛን ሰዓት የሽግግር ኳስ ይመጣል እንጂ ሌላ ችግር ኖሮት አይደለም። እኛ በማጥቃት ክልል በመስመር ውስጥ ቶሎ ቶሎ ስለምንሄድ የዛን ሰዓት ክፍተቶች ስላሉ ሽግግሮችን እየተጠቀሙ እንጂ ክፍተቶች ኖረውብን አይደለም።

ስለጨዋታው ክብደት

“ አዎ ከባድ ጨዋታ ነው። መጀመርያም ስንገባ ተናግሬአለሁ። ሁሉም ቡድኖች ለእኛ የሚዘጋጁት ፤ ከእኛ ጋር ሲጫወት ቀላል ቡድን የለም። ከእኛ ችግር ተነስተን ብዙ አደጋዎች አልፈጠርንም። ብዙ የሄድንባቸው ኳሶች በትክክል መስመራቸውን ጠብቀው አይደለም የሄዱት። ሙሉ ለሙሉ ከራሳችን ችግር ሳንሸነፍ ውጤቱን ይዞ መውጣት ትልቅ ነገር ነው።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው ዕቅድ

“ ከወላይታ ዲቻ አቅም አንፃር ስናየው ይህንን ነጥብ ለማግኘት የተከተልነው አቅጣጫ ጥሩ ነበር ማለት እችላለው። ተጋጣሚያችንን ታሳቢ በማድረግ ነው ወደ ሜዳ የገባነው። በተለይ ባለፈው ከአዳማ ጋር ሲጫወቱ ሁለተኛው ደቂቃ አግብተው የቡድኑን ሞራል መጠበቅ የሚችሉበት አቅም አላቸው። ይህ ነገር በመጀመርያው አስራ አምስት ደቂቃ እንዳያደርጉ ከልክለናቸዋል። በኋላ ግን ኳሱን ተቆጣጥረን መጫወት ችለናል። ምክንያቱም ጊዮርጊስ ከራስ በነጠቀው ኳስ ነው ብዙ ጊዜ የሚያጠቃው እና እርሱን ለማድረግ ሞክረናል። ሲጠቃለል ግን ከራሳችን ጋር ስናነፃፅረው በአቅማችን ልክ ሜዳ ላይ የተገበርነው አዋጪ ነበር።

ስለመከላከል ቅርፃቸው

“ እኔ እንግዲህ በራሴ ዕቅድ በሰፊ ሜዳ በመከላከል አላምንበትም። ትልቅ ሜዳ ነው ያለነው፣ በተናጥል የምትከላከልበት እና በጠባብ ቦታ የምትከላከልበት በዘመናዊ ሥልጠና ወሳኝ ነው። በራሴ ልክ የማምነው። ስለዚህ ጊዮርጊስ ከዕረፍት በፊት ካገባብህ ውጤት የማስጠበቅ እና ተደጋጋሚ ጎል የማስቆጠር ባህሪ ስላለው ምንም ክፍተት መስጠት የለብንም። ምክንያቱም የሚሮጡ ልጆች አሉ ፣ ከርቀት የሚመቱ ፣ የቆመ ኳስ የሚጠቀሙ ልጆች ስላሉ ተጋጣሚያችንን አስበን ነው መሄድ ያለብን። የመጨረሻው 20 ደቂቃ ግን እኛ በመልሶ ማጥቃት የሄድንባቸው ዕድሎች ነበሩ ፤ አልተሳካም። ከነበረው ሚዛናዊ ጨዋታ ነጥቡ ተገቢ ነው።

በውጤቱ ደስተኛ ስለመሆናቸው

“ እኔ ደስተኛ ነኝ ፤ ምክንያቱም ሊጉ እየተጠናቀቀ ነው። ስለዚህ ከትልቅ ቡድን አንድ ነጥብ ማግኘት ቀላል አይደለም። እኛ ደግሞ በቢጫ፣ በጉዳት ተጫዋቾች እየወጡብን ነው። ይህን ታሳቢ አድርገን ይህን ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ነው። ከተጋጣሚያችን አንፃር አቅማችን ይሄ ነው። በአቅማችን ልክ ነው ያቀድነው ፤ አቻ መሆኑ ተገቢ ነው።”

ያጋሩ