በወልቂጤ ከተማ 3-1 ተመርቶ ዕረፍት የወጣው ኢትዮጵያ ቡና ምትሀታዊ በሆኑ የመጨረሻ 12 ደቂቃዎች 4-3 ማሸነፍ ችሏል።
ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን የረታበትን አሰላላፍ ሳይቀይር ወደ ሜዳ ሲገባ ወልቂጤ ከተማዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ሮበርት ኦዶንካራን በሰዒድ ሀብታሙ ፣ ተስፋዬ ነጋሽን በዮናታን ፍሰሀ እንዲሁም ዮናስ በርታን በአቡበከር ሳኒ ምትክ ተጠቅመዋል።
እጅግ አዝናኝ የነበረው ጨዋታ በግብ ጀምሮ በግብ የትቋጨ ነበር። ገና በ12ኛው ሰከንድ ጫላ ተሺታ አበበ ጥላሁን ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ኳስ በአግባቡ ሳይቆጣጠር ደርሶ በማስጣል የዓመቱን ፈጣን ጎል አስቆጥሯል። ከግቡ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ ተቆጣጥረው ምላሽ ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ ባደረጉት ከባድ ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
ወልቂጤዎች ፊት ላይ የቡናን ተጫዋቾች በተናጠል ጫና ውስጥ በመክተት ይበልጥ አደገኛ ሆነው ሲታዩ 12ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በረከት አማረ ላይ በፈጠረው ጫና ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ ሳይሳካለት ቢቀርም ተከታዩ ጥረቱ ግን ፍሬ አፍርቶለታል። በዚህም በተመሳሳይ አጥቂው ሳጥኑ መግቢያ ላይ የአብቃል ፈረጃን ለመንጠቅ ተቃርቦ ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ራሱ በመምታት 20ኛው ደቂቃ ላይ የወልቂጤን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።
በመቀጠል ሰፊ የኳስ ቁጥጥርን ይዘው ወደ ወልቂጤ ከተማ ሳጥን መጠጋት የጀመሩት ቡናዎች ከወልቂጤ የሚሰነዘረው ጥቃት ጋብ ቢልላቸውም የሚፈልጓቸውን የመጨረሻ የግብ አጋጣሚዎች ሳይፈጥሩ ቢቆዩም ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ዕድል አግኝተዋል። በዚህም በቡና ቅብብሎች ውስጥ ከአስራት ቱንጆ የተነሳውን ኳስ በኃይሉ ተሻገር ሳጥን ውስጥ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር 31ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎታል።
ሆኖም ቡናዎች ተረጋግተው ሁለተኛ ጎል ወደሚያስገኝላቸው የጨዋታ ቁጥጥር ብልጫ ከመመለሳቸው በፊት ወልቂጤዎች ሌላ ምላሽ ሰጥተዋል። የሰራተኞቹ አማካዮች መሀል ሜዳ ላይ የተቀባበሉትን ኳስ ሀብታሙ ሸዋለም በድንቅ ሁኔታ በተከላካዮች መሀል ሰንጥቆለት ጌታነህ ከበደ በቀኝ ከጠባብ አንግል ሦስተኛ ግብ አድርጎታል።
በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው በንፅፅር ቀዝቀዝ ብሎ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን በማንሸራሸር ሁለተኛ ግብ የሚያስገኝላቸውን ቀዳዳ ለማግኘት ሲጥሩ በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ንክኪዎቻቸው በአስራት ቱንጆ እና አቡበከር ናስር አማካይነት ሳጥን ውስጥ አደጋ ለመጣል ተቃርበው ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። በአመዛኙ ከኳስ ጀርባ የነበሩት ወልቂጤዎችም የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ለማግኘት ጥረት አድርገው ጨዋታው ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስም የቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲቀጥል ቡድኑ ከፍ ያለ ጫና ቢያስድርም ከሳጥን ውጪ እና ከቆመ ኳስ ያደረጋቸው ሙከራዎች ውጤታማ አልሆኑም። ይልቁኑም ወልቂጤዎች ከቡና ተከላካይ ጀርባ በተከታታይ የገቡባቸው አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። 56ኛ እና 58ኛ ደቂቃ ላይ ከረመዳን የሱፍ እና አብዱልከሪም ወርቁ የተነሱ ረጅም ኳሶች ጫላ ተሺታ በቀኝ አቅጣጫ ሰብሮ እንዲገባ ቢያደርጉትም ወደ ግብ እና ወደ ጌታነህ ከበደ ለማድረስ ያደረጋቸው ጥረቶች ሳይሰምሩ ቀርተዋል።
የቡና የኳስ ቁጥጥር 62ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ ሲቀርብ አቡበከር ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ በድንቅ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብ ሲልከው ዊሊያም ሰለሞን ከግቡ አፋፍ ላይ ተንሸራቶ ለማስቆጠር ቢቃረብም ካሷን ሳያገኛት ቀርቷል። ጨዋታው በተመሳሳይ አኳኋን ሲቀጥል ቡና ከቅጣት ምት እና ከሳጥን መግቢያ ላይ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጪ ወደ ጥንቃቄ ያደላው ወልቂጤ ከተማን አስከፍቶ መግባት አቅቶት ቢቆይም ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሁለት ግቦችን አከታትሎ በማስቆጠር ወደ አቻነት መጥቷል።
79ኛው ደቂቃ ላይ ከቡድኑ የግራ ጥቃት የአብቃል ፈረጃ ሳጥን ውስጥ አቡበከር ናስር ከአማኑኤል ዮሐንስ ተቀብሎ ያመቻቸለትን ኳስ ከመረብ ማገናኘት ሲችል ወልቂጤዎች ጨዋታውን ከመሀል ጀምረው እምብዛም ሳይቆይ ታፈሰ ሰለሞን ከተከላካዮች ጀርባ ለአቡበከር ያደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ይዞ በድጋሚ በግራ አቅጣጫ አጥቂው አፈትልኮ በመውጣት ቡድኑን አቻ አድርጓል።
የጨዋታው ድራማዊ ትዕይንት እና የኢትዮጵያ ቡናዎች ምልሰት ግን በዚህ ያበቃ አልነበረም። በግቦቹ መረጋጋታቸውን ያጡት ወልቂጤዎች ምላሽ ለመስጠት ወደ ጨዋታው ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካ ቡናማዎቹ ማጥቃታቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ 87ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳጥን ውስጥ ባገኘው ሌላ ዕድል ለማስቆጠር ተቃርቦ ውሀብ አዳምስ ተደርቦ አግዶታል። ሆኖም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቡናዎች በድጋሚ በግራ ጥቃት ወደ ወልቂጤ ሳጥን ደርሰው አስራት ቱንጁ ድንቅ ከነበረው ከአቡበከር የደረሰውን ኳስ በግራ እግሩ ከመረብ አገናኝቶ የኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በአስገራሚ ሁኔታ ውጤት መቀልበስ በቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 4-3 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ34 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልቂጤ ከተማ በ29 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል።