ሉሲዎቹን በሴካፋ ውድድር የሚመራው አሠልጣኝ ታውቋል

በሴካፋ የሴቶች ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን የሚመራ አሰልጣኝ መምረጡን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የምስራቅ እና መካከለኛው የእንስቶች ዋንጫ ውድድር በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በውድድሩ የሚሳተፉ አንዳንድ ብሔራዊ ቡድኖች ቀደም ብለው ዝግጅት የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ግን እስከ አሁን አሠልጣኝ ሳይሾም ቆይቶ ነበር። ለውድድሩ በቅርቡ ዝግጅት የሚጀምረው ቡድኑ ለዚህም እንዲረዳው የ20 ዓመት በታች ቡድኑን አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተጨማሪ ኃላፊነት ይዞ እንዲሰራ መምረጡን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫን ያሸነፈው አሠልጣኝ ፍሬው በዓለም ዋንጫ ማጣርያም እስከ መጨረሻው ዙር መድረሱ የሚታወስ ሲሆን ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ እንዲያደርግ ኃላፊነት እንደተሰጠው ከመገለፁ በቀር የኮንትራቱ ዝርዝረ ይፋ አልሆነም።

ኢትዮጵያ በምድብ ለ ከታንዛንያ ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን መደልደሏ ይታወሳል።