የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 4-3 ወልቂጤ ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና ከእረፍት መልስ የተለየ አቅሙን በማሳየት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ከያዘበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ሁለቱ አጋማሾች…?

እንቅስቃሴውን በተመለከተ ብዙም የተለየ ነገር የለም፡፡ የመጀመሪያው ግማሽ ላይ እንደ ተጀመረ የሰራነው ስህተት አለ፡፡ ከዛ በኋላ እንደገና በቅጣት ምት የተገኘውም ኳስ ልጆቹ በሸፈኑበት በኩል ነው የገባሁ፡፡ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ስንመለከት ስህተት ነው የሚፈልጉት። ያንን ስህተት ተጠቅመው በተከፈተው ቦታ ለማስቆጠር ነው ሀሳባቸው፡፡ ስንጫወት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን። ያለውን ነገር ጠብቀን ማስቀጠልም ይኖርብናል፡፡ በዚህም የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንደምንችል ነበር የተነጋገርነው፡፡ ጥሩ ነበር የነበረው፡፡

4 ጎሎች ሊያስቆጥሩ ስለቻሉበት ምክንያት…?

አንዱ የተለወጠው ነገር ከዚህ በፊት በደንብ የማናደርገው መስመሩን በደንብ መጠቀም ነው። ይሄ ሜዳውም ሰፊ ስለሆነ ተጋጣሚ የመጨረሻው እኛም ብንሆን ሌላም ቡድን የመጨረሻው ጎሉን መከላከልን ነው፡፡ ስለዚህ ስለሚያጠቡ መስመሩን በደንብ መጠቀም ነው፡፡ መስመሩን ከተጠቀምን የመሀሉን ልናገኘው እንችላለን የሚል ነው፡፡ ጥሩ ነበር፡፡

ስለ ተከላካይ ድክመት…?

የግንዛቤ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ መጀመሪያ ከታፈሰ የተወሰደው ኳስ አበበን ብቻ ነው የተመለከተው፡፡ የእነርሱ ተጫዋች በቀኝ መስመር የሚጫወተው ጫላ አጥብቦ ቆሟል እና እርሱንም ግምት ውስጥ መክተት ነበረበት፡፡ ያን ግምት ውስጥ ያለ መክተት ነው፡፡ የግንዛቤ ጉዳይ ነው የሚስተካከል ነው፡፡

አሠልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ሁለቱ አርባ አምስቶች…?

የመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ ያሰብነውን አሳክተናል፡፡ የፕረሲንግ አጨዋወታችንን ወደ ሚድፊልድ አቅርበነው እየነጠቀናቸው ነበር አደጋ ለመፍጠር የፈለግነው። ያንን አሳክተናል፡፡ ሁለተኛ አርባ አምስት ላይ ግን ቡድናችን በአጠቃላይ ያልተቀናጀ ነበር፡፡ እነርሱ 3ለ1 እየተመሩ ነው፡፡ ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ሙሉ በሙሉ ነቅለው ማጥቃት ነው የሚያደርጉት። ይሄንን የእነርሱን አስተሳሰብ ማቆም የሚያስችል ዝግጅት አልነበረንም ፡፡ እንደ አጠቃላይ ያልተቀናጀ ነበር ሁለተኛው አርባ አምስት፡፡

የሽንፈቱ ምክንያት…?

የመጀመሪያውን አስር ደቂቃ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ሁለት ንፁህ ኳሶች አምክነናል፡፡ በተለይ ጫላ ያገኛቸውን ዕድሎች ከጌታነህ ጋር ያለው ግንኙነት ትክክለኛ ባለመሆኑ የሳትናቸውን ሁለት ዕድሎች አሉ፡፡ እነርሱን አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ ምናልባት ኢትዮጵያ ቡና የሚነሳበት ዕድል አይኖርም ነበር፡፡ ከዛ በኋላ እነርሱ ያገኙትን ዕድል ሲጠቀሙ ወደ ጨዋታው እየገቡ መጡ፡፡

በሁለተኛው አርባ አምስት ስለታየው ድካም…?

አዎ፡፡ የተወሰነ ድካም አይቻለሁ፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በጣም ሀይል የሚፈጅ የነበረው ጨዋታ ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን ማስካከል የሚያስችል የአቅም ችግር ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ነበረብን፡፡ ይሄን በቅያሪ ለማስተካከል ሞክረናል፡፡