የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

በ15ኛው ሳምንት ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ትኩረት ይሰብ የነበው የንግድ ባንክ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ስምንት ሰዓት መከናወን የሚገባው የባህር ዳር ከተማ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ሰበታዎች በባቱ ከተማ በቀጠለው የሁለተኛው ዙር ውድድር ሁለተኛ ጨዋታ ካከናወኑ በኋላ የፋይናስ ችግር አጋጥሟቸው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ ለሁሉም ቡድን ፎርፌ የሚሰጥ በመሆኑ ለባህር ዳሮችም የእርስ በእርስ ጨዋታቸውን አድርገው ሙሉ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎል በመያዝ ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል።

 የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታን በኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት ተካሂዶ ንግድ ባንኮች ሲዳማ ቡናን አንድ ለምንም አሸንፈዋል

እንደጨዋታው ተጠባቂነት ጥራት ያለው እግርኳስ ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመሀል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ ተፎካክረዋል። ንግድ ባንኮች ኳሱን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ይዘው በመውጣት በሂደት የሲዳማ የግብ ክልል ቢደርሱም ግልፅ የጎል ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ትኩረት ያደረጉ ኳሶችን ከተከላካይ ጀርባ በመጣል የጨዋታውን የበላይነት ለመውሰድ ሲዳማ ቡናዎች ቢታትሩም በተሳሳይ የጎል አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸው ነበር።

ሆኖም በመጀመርያው አጋማሽ እጅግ ለጎል የቀረበውን ሙከራ ሲዳማ ቡናዎች በ34ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ሲዳማዎች ያገኙትን ቅጣት ምት በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ይስሐቅ ካኖ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ የመታውን በግሩም ሁኔታ ግብ ጠባቂው አስቻለው በየነ ወደ ውጪ አውጥቶበት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ ንግድ ባንኮች ጎል ማስቆጠር መቻላቸው የጨዋታውን ግለት ከፍ አድርጎታል። ሚሊዮን ኃይሌ ከግራ መስመር ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ ዳዊት ዮሐንስ በግንባሩ በመግጨት በ47ኛው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ዳዊት ጎል በማስቆጠር ብቻ ሳይገደብ በማጥቃቱም ወደ ኋላ በመመለስ በመከላከሉ ረገድ ቡድኑን ይረዳ የነበረበት መንገድ ለወደፊት ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ እንደሆነ ያሳየ ነበር። ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በተለይ የሲዳማን የግራ መስመር የማጥቂያ መንገድ በማድረግ በሚሊዮን አማካኝነት እንደልብ ቢመላለሱበትም የሚሻገሩት ኳሶች ተቀባይ ባለማግኘታቸው በተደጋጋሚ ይባክኑ ነበር።

የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር የንግድ ባንኮችን ማፈግፈጋቸውን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጎል ፍለጋ ጥረት አድርገዋል።

75ኛው ደቂቃ ናትናኤል ደስታ ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው የያዘበት እና ራሱ በድጋሚ በ82ኛው ደቂቃ ከመስመር የተቀበለውን አምስት ከሀምሳ ውስጥ ተከላካይ አሸማቆ በማለፍ ራሱን ነፃ በማድረግ ጎል አስቆጠረ ሲባል ያልተጠቀመበት ለሲዳማ ቡና የሚያስቆጭ ነበር። በመጨረሻው ደቂቃ ሌላ የጎል አጋጣሚ ዮናስ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም የዕለቱ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ አስቻለው በየነ እንደምንም አድኖበት ጨዋታው አንድ ለምንም ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ደረጃውን በማሻሻል ወደ ዋንጫው ፉክክር ራሱን ሲያስገባ ሲዳማ ቡና ከመሪነት ደረጃው በአንድ ነጥብ ዝቅ በማለት ሁለተኛ ደረጃ ሊቀመጥ ችሏል።