ኢትዮጵያ ግብፅን የምትገጥምበት ስታዲየም ታውቋል

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በካፍ ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያቸውን ሁለተኛ ጨዋታ የሚያደርጉበት ስታዲየም ታውቋል።

ከቀናት በፊት በእገዳ ላይ የቆየው የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም በካፍ ባለሙያ ተገምግሞ አህጉራዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ አሁንም ብቁ አለመሆኑ መገለፁ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሜዳ ጨዋታዎቿን የት ልታደርግ እንደምትችል ሲጠበቅ ነበር።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምሽቱን በድረገፁ ባስታወቀው መሰረትም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባደረገው ስብስባ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ያደርጉት የነበረውን የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከግብፅ ጋር በማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ በሚገኘው እና አሁን ላይ በካፍ በፀደቀው ቢንጉ ስታዲየም እንዲያደርጉ ውሳኔ አሳልፏል። ፌዴሬሽኑ እንዳለው ይህ ውሳኔ በማላዊ መንግሥት እና እግርኳስ ፌዴሬሽን ይሁንታን ያገኘ ሲሆን ካፍም በሀሳቡ እንደተስማማ የሚገልፅ ደብዳቤ ልኳል።

በመሆኑም ዋሊያዎቹ ማጣሪያውን ሲጀምሩ ግንቦት 25 ላይ ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን የሜዳ ውጪ ጨዋታቸውን ከካደረጉ በኋላ እዛው ቆይተው ከአራት ቀናት በኋላ ከፈርኦኖቹ ጋር እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

ያጋሩ